ኑ እና ቤታችሁን ጎብኙ – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

ጥር 16/2014 (ዋልታ) ከ57 ዓመታት በኋላ ነባር ገፅታውንና ቅርስነቱን ሳይለቅ መሰረታዊ እድሳት የተደረገለት እድሜ ጠገቡ የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ህንፃ ነዋሪዎች እንዲጎበኙ የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ጋበዙ።
ህንፃው ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና እና ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት ዛሬ ከሰዓት ይመረቃል።
ህንፃው የታደሰው ባማረና ምቹ አገልግሎት መስጠት በሚያስችል፣ ዘመናዊነትን በተላበሰ፣ ብሎም የከተማዋን ደረጃ በሚመጥን መልኩ መሆኑን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል።
“ከተማዋ የኢትዮጵያ ብሎም የአፍሪካዊያን መዲና፣ የዓለም ዐቀፍ ተቋማት መቀመጫና ዲፕሎማቲክ ማዕከል በመሆኗ ስሟን የሚመጥኑ ተግባራትን ማከወናችንን እንቀጥላለን” ብለዋል ከንቲባዋ በማኅበራዊ ትስስር ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት።
“ይህ ህንፃ የትውልዱ ታሪክም፣ ሃብትም፣ ቅርስም፣ ገፀ በረከትም ነው” ያሉት ከንቲባዋ ህንፃው ከነገ ሰኞ ጀምሮ ለሕዝብ ክፍት የሚደረግ በመሆኑ “ኑ እና ቤታችሁን ጎብኙ” በማለት ጋብዘዋል።