ኒዮርክ ታይምስና አሶሼትድ ፕሬስ ህወሓት ህጻናትን ለውትድርና መጠቀሙን አሞካሽተው መዘገባቸው የሚያሳዝን ነው – ቢልለኔ ስዩም

ቢልለኔ ስዩም

ሐምሌ 08/2013 (ዋልታ) – ኒዮርክ ታይምስና አሶሼትድ ፕሬስ ህወሓት ህጻናትን ለውትድርና መጠቀሙን አሞካሽተው መዘገባቸው የሚያሳዝን ነው ሲሉ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬተሪ ቢልለኔ ስዩም ገለጹ።

ቢልለኔ በትዊተር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት ኒዮርክ ታይምስ እና አሶሼትድ ፕሬስ በዘገባዎቻቸው ላይ ህወሓት ህጻናትን ለውትድርና መጠቀሙን አሞካሽተው ማቅረባቸው የሚያሳዝን ነው ሲሉ ገልጸዋል።

አሶሸትድ ፕሬስ እና ኒውዮርክ ታይምስ በተደጋጋሚ የአሸባሪው ህወሓትን የተመለከቱ ሚዛናዊ ያልሆኑ የአንድ ወገን ዘገባዎችን ሲሰሩ ቆይተዋል።

በተለይም የሀገር መከላከያ ሰራዊት የመንግስትን የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ ተከትሎ ከክልሉ ከወጣ በኋላ በንጹሀን ዜጎች ላይ እንዲሁም በኤርትራዊያን ስደተኞች ላይ የሚፈጸሙ ግድያዎችንና ዝርፊያዎችን ሲዘግቡ አይታዩም።

ከሰሞኑም አሸባሪው ድርጅት የመንግስትን የተናጠል የተኩስ አቁም ርምጃ ወደ ጎን በማለት በአማራና በአፋር ክልል በኩል ጥቃት እየፈጸመ መሆኑን በማወደስ ህወሓት ግዛቱን አስመለሰ የሚል ዘገባዎች ላይ ተጠምደው ይታያሉ።

የህጻናት “ወታደሮችን” ጉዳይ በመተቼት ሚዲያዎች ከመስራት ይልቅ ህወሃትን በአለም አቀፍ የጦር ወንጀል ሊያስጠይቅ የሚችል ተግባር ሚዲያዎች እያበረታቱ ነው ያሉት የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ባለሙያው አቶ ገዛሀኝ በርሄ፣ አለም አቀፍ ሚዲያዎች ህወሓት ህጻናትን ለጦርነት ማሰለፉን በዘገባዎቻቸው ማጋለጥና ድርጊቱ ወንጀል መሆኑን ከመዘገብ ይልቅ ህጻናቱን የህወሓት የህዝብ ድጋፍ ማሳያ አድርገው መዘገባቸው የጋዜጠኝነት ስነ ምግባርና  አለም አቀፉን የጦር ህግጋት  የጣሰ መሆኑን ገልጸዋል።

ከሰአታት በፊት የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በሰጡት መግለጫ፣ አንድ አንድ ድርጅቶች አገር ውስጥ ሆነው ርዳታ እንዲያስተባብሩ ከመደቧቸው ግለሰቦች ውጭ በርቀት ሆነው ከርዳታ ይልቅ ፕሮፖጋንዳ የማስተባበር የኢትዮጵያን መንግስት የማዋከብና የማጠልሸት ዘመቻ በስፋት ከፍተው እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም ብዙዎች ሲጠይቁትና ሲጓጉለት የነበረው የሰላም ውሳኔ በመንግስት ተወስኖ እያለ ውሳኔውን ከማመስገን ይልቅ ውሳኔውን በማሳነስ አፍራሽ በሆነ መልኩ እየተንቀሳቀሱ ያሉ አገራትና ግለሰቦች መኖራቸውን በመጥቀስ የምዕራባዊያኑ ሚዲያዎችም ያሉ አዎንታዊ መሻሻሎችን ከመዘገብ ይልቅ በተቃራኒው እየሄዱ መሆኑን መግለጻቸውን አስታውሶ ኢፕድ ዘግቧል።