ጥምር ጦሩ መርሳን ተቆጣጥሮ ወደ ወልዲያ እየቀረበ ነው

ታኅሣሥ 8/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ የጸጥታ ኃይሎች ጥምረት መርሳና ግራናን በመቆጣጠር ወደፊት እየገሠገሠ ነው፡፡

የአትዮጵያ የጸጥታ ኃይሎች ጥምረት በቆቦ ግንባር ቀደም ብሎ የዞብል ከፍተኛ ቦታዎችን ተቆጣጥሮ የነበረ ሲሆን፣ በራያ ሰሜናዊ አቅጣጫ ያሉትን ከፍተኛ ቦታዎችን ጨምሮ ተቆጣጥሯል፡፡

በዞብል ደቡብ አቅጣጫ ደግሞ የጉራ ወርቄ አካባቢዎችን ተቆጣጥሮ የነበረው የወገን ጦር አሁን ደግሞ የጉራ ወርቄ ከፍተኛ ሰንሰለታማ ቦታዎችን ሙሉ በሙሉ በማጽዳት፣ ቀደም ብሎ የተቆረጠውን የወልድያ መቀሌ መሥመር አሰፋፍቶ፣ ወደ ወልድያ በቅርብ ርቀት እየገሠገሠ ይገኛል፡፡

ባለፈው ጊዜ ውጫሌ ከተማን ነጸ ያወጣው የወገን ጦር፣ በዚሁ ግንባር የውጫሌ ወረዳን ሙሉ በሙሉ በመቆጣጠር የውርጌሳ፣ የሊብሶ፣ የግራና፣ የመርሳ፣ የኪሌ፣ ከተሞችንና በሰሜን ወሎ የሐርቡ ወረዳን ከፍተኛ ሰንሰለታማ ተራሮችን በእጁ አስገብቷል፡፡

በእነዚህ የማጥቃት እንቅስቃሴዎች ጀግኖቹ የወገን ጥምር ጦር በንሥሮቹ አየር ኃይላችን በመታገዝ ጠላትን ከመርሳ በስተጀርባ ቆርጦ በመግባት፣ በውጫሌና ውርጌሳ መካከል የነበረውን ጠላት ሙሉ በሙሉ ደምስሰውታል፤ ምርኮኛና ቁስለኛም አድርገውታል፡፡

የአካባቢው ሕብረተሰብ ከወገን ጥምር ጦር ጋር በመቀናጀት፣ እግሬ አውጪኝ ብሎ የሚሸሸውን ጠላት ከየጢሻው እየመነጠረ በመደምሰስ አኩሪ ጀብድ ፈጽሟል፡፡

ጠላትም የዘረፈውን ንብረትና ተተኳሾቹን ፈጽሞ ይዞ እንዳይወጣ አድርጎታል፡፡

የወገን ጥምር ጦር በወልድያና ሐራ ከተሞች መካከል የሚገኘውንና መውጫ ያጣውን ጠላት ለመደምሰስ፣ በተቀናጀና በተደራጀ መንገድ ወደ ፊት እየገሠገሠ ነው፡፡