ኢትዮጵያ በስኬት ባጠናቀቀችው ህግ የማስከበር ዘመቻ እና የአለም አቀፍ ሚዲያዎች የተሳሳተ ዘገባ በጋዜጠኞች እና በሚዲያ ባለሞያዎች እይታ ምን ይመስላል ስንል በሚዲያው ዘርፍ ለረዥም አመት ያገለገሉ ጋዜጠኞችን አነጋግረናል፡፡
በዚህም ህግ የማስከበር ስራውን ኢትዮጵያ ስታከናውን እውነታ ላይ ያልተመሰረተ ዘገባን ለአለም ህዝብ ለማድረስ ሲጥሩ እንደነበረ ሁሉ ዛሬ ላይ ህግ የማስከበር ስራው ተጠናቆ ወደ መልሶ ግንባታ ምዕራፍ የኢትዮጵያ መንግስት ሲገባ ጆሮ ዳባ ልበስ ብለው ሲዘግቡት አልታየም ብለዋል፡፡
ይህም ከጋዜጠኝነት መርህ ውጪ የአድሎ እና እውነታነት የሌለው ስራ ሲሰሩ ለመቆየታቸው ማሳያ ነው ሲሉ ጋዜጠኛ ቤኛ ሲሜሶ እና ጋዜጠኛ እሸቱ ገለቱ ከዋልታ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል፡፡
ሃያላን የሚባሉ ሀገራት ኢትዮጵያ ላይ የደረሰውን አይነት ጥቃት በታሪካቸው አስተናግደው ምላሻቸው ኢትዮጵያ አሁን ከወሰደችው ህግ የማስከበር ስራ የተለየ አይደለም ያሉት ጋዜጠኞቹ ሌሎች ሀገራት የማያደርጉትን ድርድር ነበር ኢትዮጵያ ማድረግ አለባት ብለው ሲሞግቱ የነበረው ብለዋል፡፡
እነዚህ ሚዲያዎች ሌላ አጀንዳ እንዳላቸው ምስክር የሚሆነው ህግ ከማስከበር ዘመቻው በኋላ በክልሉ እየተሰሩ ያሉትን የመልሶ ግንባታ ስራዎች አለመዘገባቸው ነው ብለዋል፡፡
(በሜሮን መስፍን)