አልማ በአጣዬና አካባቢው ለተፈናቀሉ ወገኖች 30 ሚሊየን ብር የሚገመት ድጋፍ አደረገ

ግንቦት 13/2013 (ዋልታ) የአማራ ልማት ማህበር (አልማ) በአማራ ክልል በአጣዬና አካባቢዉ ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ተፈናቅለው በመጠለያ ለሚገኙ ወገኖች 30 ሚሊየን ብር ግምት ያለው የምግብና ሌሎች ቁሳቁሶች ድጋፍ ማድረጉን አስታወቀ።

ማህበሩ የምግብና ቁሳቁስ ድጋፉን ያደረገው ከመንግስት፣ ከልማትና ከግል ድርጅቶች በማሰባሰብ ነው።

የአልማ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መላኩ ፋንታ በደብረብርሀን ከተማ ድጋፉን ሲያስረክቡ እንደገለጹት፤ ድጋፉ ተፈናቃዮችን ለማቋቋም የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ነው።

በክልሉ በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ አደጋዎች የሚደርሱ ሰብአዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶችን ለመቀነስ አልማ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸው፤ አሁንም በአጣዬና አካባቢው ለተፈናቀሉ ወገኖች 64 ሺህ 240 የቤት ክዳን ቆርቆሮ፣ 6 ሺህ እሽግ ሚስማርና 15 ሺህ ሊትር ዘይት፣ ፍራሽ፣ ብርድልብስና አንሶላ ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል።

የአካባቢዉ የፀጥታ ሁኔታ እስከሚረጋገጥ ድረስና ነዋሪዎች ወደ ቀደመ አኗኗራቸው እስከሚመለሱ ድረስ ህብረተሰቡ ድጋፍ እንዲያደርግ አቶ መላኩ ጠይቀዋል።

የአዲስ አበባ፣ የባህርዳር፣ የጎንደርና የሌሎች አካባቢዎች በጎ ፈቃደኛ ግለሰቦችም በድጋፉ መሳተፋቸውን ጠቁመው፤ ኬኬ ሀለፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበርና ሌሎች ባለሃብቶችንም ላደረጉት ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ ገብረፃዲቅ በበኩላቸው “አልማ ያደረገው ድጋፍ ክረምቱ ከመግባቱ አስቀድሞ ተፈናቃዮችን ወደ ቦታቸው ለመመለስ የሚያግዝ ነው” ብለዋል።

ተፈናቃዮችን ወደ ቀዬአቸው በወቅቱ መመለሱ ለመኸር እርሻ እንዲዘጋጁ ከማገዙም በላይ የአካባቢውን ሰላም ለማስጠበቅ ሚናዉ የጎላ መሆኑን አስታውቀዋል።

በዞኑ የሚገኙ ከ253 ሺህ ህዝብ በላይ ተፈናቃዮችን ወደ ቀድሞ ቦታቸው ለመመለስ የክልሉ መንግስት የድጋፍ ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል።