አልሸባብ የሽብር ተልዕኮ የሰጣቸው 6 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

አልሸባብ የሽብር ተልዕኮ የሰጣቸው ግለሰቦች

ግንቦት 6/2014 (ዋልታ) በሶማሊያ በሚንቀሳቀሰው አልሸባብ የሽብር ቡድን ሰልጥነው በኢትዮጵያ የጥፋት ተልዕኮ ተሰጥቷቸው ወደ ስምሪት ሊገቡ የነበሩ ስድስት ተጠርጣሪ ግለሰቦች በአዲስ አበባ ከተማ እና በኦሮሚያ ክልል በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አስታውቋል።

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት እንዳስታወቀው፤ ጃፋር ያያ ረቢ፣ ሙሳ ቀና ቤኛ፣ አደም ቤካ ኬነሳ፣ አብዱራዛቅ ሻፊ አሊ፣ አብዱል ከሪም አህመድ ኩሽዬ እና ዘቢር ጂያድ ከድር የተባሉት ተጠርጣሪዎች በሶማሊያ በሚንቀሳቀሰው የአልሸባብ የሽብር ቡድን ተመልምለው በኢትዮጵያ በህቡዕ ድጋፍ በሚያደርጉ አካላት አማካኝነት ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል ተሰባስበው ከየካቲት 2 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ ወቅቶች ወደ ሶማሌ እንዲገቡ ተደርጓል።

በዚያም የሽብር ጥቃት ለመፈጸም የሚረዱ የተለያዩ ስልቶችንና የቡድኑን አስተምህሮ የተመለከቱ ስልጠናዎች ለሶስት ወራት ወስደዋል።

በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የሽብር ጥቃት እንዲፈጽሙ የተመለመሉትና ስልጠና የወሰዱት ስድስቱ ተጠርጣሪ ግለሰቦች ግንቦት 3 ቀን 2014 ዓ.ም ከሶማሊያ ተነስተው በሞያሌ በኩል ወደ ሀገር ውስጥ መግባታቸው የተመላከተ ሲሆን ፤ ሚያዚያ 4 እና 5 ቀን 2014 ዓ.ም በሁለት ቡድን ተከፍለው ወደ ጅማ ለመሄድ አቅደው እንደነበርም ጠቁሟል።

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት በአልሸባብ ቡድን ላይ በሚያደርገው ክትትልና የመረጃ ስምሪት መነሻነት የጥፋት እቅዱን ከውጥኑ ጀምሮ ሲከታተል እንደነበር ያመለከተው መግለጫው፤ የሽብር ቡድኑ በኢትዮጵያ ያለውን የግንኙነት መረብ ጭምር ለማወቅና እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል መረጃ ሲሰበሰብና ሲጠናቀር ቆይቶ ከጸጥታ አካላት ጋር በተከናወነ ኦፕሬሽን ተጠርጣሪዎቹ በአዲስ አበባ ከተማ እና በኦሮሚያ ክልል በቁጥጥር ስር እንዲውሉ መደረጉን ገልጿል።

የሽብር ቡድን አባላት በቁጥጥር ስር በዋሉበት ወቅት የተለያዩ የጦር መሣሪያዎች፤ የሽብር ቡድኑን አስተምህሮ ለማስረጽ ጥቅም ላይ የሚውሉ ሰነዶች እና ሌሎችም ተቀጣጣይ ቁሶች ተይዘዋል።

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት በአዲስ አበባና በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሽብር ጥቃት ለመፈፀም ዝግጅት ሲያደርጉ የነበሩ የአልሸባብ አባላትን ከሶማሌና ከኦሮሚያ ክልሎች የጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር ባከናወናቸው ኦፕሬሽኖች 34 የሽብር ቡድኑ አባላት በሚያዝያ 2014 ዓ.ም በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ማድረጉን አስታውሷል።

በተከታታይ በተደረጉ ኦፕሬሽኖችም ተጨማሪ 11 በሽብር ጥቃት የተጠረጠሩ ግለሰቦች ተይዘው እንደነበር በመጥቀስ፤ በአጠቃላይ 45 የሽብር ቡድኑ አባላት የሽብር ጥቃቶችን ለመፈጸም ካዘጋጇቸው ቦንቦች እንዲሁም ክላሽንኮቭ ጠመንጃዎች፣መትረየሶች ፣ አርፒጂ የጦር መሣሪያዎች እና መሰል ጥይቶች ጋር ከክልልና ከፌደራል ፀጥታ ኃይል ጋር በመሆን በህግ ቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው ይገኛል።