አመራሩ የሰውን ህይወትና ንብረት በብስለት የመምራት ትልቅ ኃላፊነት እነዳለበት ሌ/ጀኔራል ዘውዱ አሳሰቡ

የካቲት 24/2014 (ዋልታ) የሰራዊቱ አመራር በሠላም ወረዳም ይሁን በጦርነት ወቅት የሰውን ህይወትና የመንግሥትን ንብረት በብስለት የመምራት ትልቅ ኃላፊነት እንዳለበት የማዕከላዊ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀኔራል ዘውዱ በላይ አሳሰቡ።

ሰራዊቱ በሄደበት ሁሉ ግዳጁን በጀግንነት የሚፈፅምና ምስጉን መሆኑን የጠቀሱት ሌተናል ጀኔራሉ ይህን ለማስቀጠል አመራሩ ኃላፊነት አለበት ብለዋል።

የማዕከላዊ ዕዝ ከፍተኛ አመራሮች ዕዙ የተሠጠውን አገራዊ ተልዕኮ በስኬታማነት ለመፈፀም የሚያስችለውን የተሟላ ዝግጁነትን ከማረጋገጥ ጎን ለጎን ዲስፕሊኑ የተጠበቀ ተተኪ ሠራዊት ለመገንባት በወታደራዊ ባህልና ጨዋነት ዙሪያ ውይይት አካሂደዋል።

በሳል አመራር ብቁ የሠራዊት አባላትን ለማፍራት አይቸገርም ብለዋል።

የሀገሪቱን የእድገት ጉዞ ለማደናቀፍ የማይተኙ የውጭ ኃይሎችና የአገር ውስጥ አሸባሪ ቡድኖች ከጥፋት አላማቸው እስካልተቆጠቡ ድረስ አመራሩ ራሱንና የሚመራውን አባል አዘምኖ እንደ ከዚህ ቀደሙ የጀግንነት ታሪኩን ሊያስቀጥል እንደሚገባው አስገንዝበዋል።

በተያያዘ በጦላይ የከፍተኛ ባለሌላ ማዕረግተኛ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ውጤታማ የግዳጅ አፈፃፀም ለነበራችውና የመቆያ ጊዜያችውን ለሸፈኑ የሰራዊት አባላት ማእረግ አልብሷል፡፡

የትምህርት ቤቱ ዋና አዛዥ ብርጋዴል ጄኔራል ጡምሲዶ ፊታሞ ጀግናው መከላከያ ሰራዊታት የአሸባሪውን ቡድን አከርካሪ በመምታት ኢትዮጵያ አንፃራዊ ሰላም እንድታገኝ ጠንካራ ሰራዊት በማሰልጠንና በመገንባት ላደረጉት ጥረት ምስጋና ማቅረባቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡