አሚኮ ለውጡ በአማራ ክልል እንዲቀጣጠል በማድረግ አኩሪ ታሪክ የፈጸመ ሚዲያ ነው – ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)

ሰኔ 13/2014 (ዋልታ) አሚኮ ለውጡ በአማራ ክልል እንዲቀጣጠል በማድረግ አኩሪ ታሪክ የፈጸመ ሚዲያ መሆኑን የኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ሚኒስትሩ አሚኮ ከትንሽ ዳስ እስከ ግዙፍ ሚዲያ መድረስ የቻለ እና የሕዝቡን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና የመልካም አሥተዳደር ችግሮች ነቅሶ በማውጣት በሕዝብ ልብ ውስጥ መግባት የቻለ ሚዲያ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

ሚኒስትሩ የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን “አሚኮ ኅብር” የተሰኘ አዲስ ቻናል የማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ነው ይሕንን የገለጹት፡፡

አሚኮ ባለብዙ የሚዲያ ልሳን ባለቤት መሆን የቻለው ጠንክሮ የሕዝብ ልሳን መሆን በመቻሉ እንደሆነ የተናገሩት ሚኒስትሩ አሁን ላይ ሚዲያዎች ላልተፈለገ ጽንፈኝነት እና አክራሪነት መጋለጡንና ሚዲያዎቹ የኅብረተሰቡን ፍላጎት በትክከል መግለጽ ያልቻሉበት ጊዜ ላይ መደረሱን ጠቁመዋል፡፡

አብዛኞቹ ሚዲያዎች ኅብረተሰብን ከማቀራረብ ይልቅ የሚያራርቁ ኅብረተሰብን አንድ ከማድረግ ይልቅ የሚበትኑ አስተሳሰቦችን በማራገብ የአድሃሪያን አስተሳሰብ እንደተጠናወታቸውም አስረድተዋል፡፡

በዚህ ሂደት አሚኮ የሕዝብ ልሳን በመሆን የሕዝብን ፍላጎት እና ትክክለኛ አመለካከት በማውጣት አኩሪ ሥራ ሲሠራ መቆየቱን ነው ያነሱት፡፡

አሚኮ ለውጡ በአማራ ክልል እንዲቀጣጠል በማድረግ አኩሪ ታሪክ የፈጸመ ሚዲያ እንደሆነም ነው ያስገነዘቡት፡፡ ለውጡ ፈር እንዲይዝ እና ሕዝቡ ለውጡን ጠብቆ እንዲዘልቅ በማድረግ አሚኮ የሠራው ሥራ የሚያኮራ እንደሆነ የገለጹት ሚኒስትሩ አሚኮ መንግሥት ሕግ በማስከበር በኩል ለሚሠራው ሥራ ትክክለኛ መረጃ በማቀበል እየሠራ በመሆኑ መንግሥት ከፍተኛ ምሥጋና አለው ብለዋል፡፡

ሚኒስትሩ ሚዲያው ዓለም ከደረሰበት የቴክኖሎጅ ደረጃ በመድረስ መንግሥት የሚያወጣቸው ደንቦች እና መመሪያዎች ከኅብረተሰቡ ደርስው ተቀባይነት እንዲኖራቸው እና ለአንድ ዓላማ በአንድነት ሕዝብ እና መንግሥት እንዲንቀሳቀሱ አሚኮ ትልቅ ኃላፊነት እንደተጣለበት አስረድተዋል፡፡

ሚዲያው ለአዎንታዊ ዘላቂ ሰላም፣ ለብልጽግና፣ ለኅብረብሔራዊ አንድነት እና በጽኑ መሠረት ላይ ለተገነባ ዴሞክራሲ ከፍተኛ ርብርብ ማድረግ እንዳለበትና ለዚህም የሚዲያ አመራሩ ስልታዊ አሠራር መከተል እንደሚጠበቅበት አስገንዝበዋል፡፡

አሁን ያለው ኅብረተሰብ አጫጭር መልዕክቶችን ሳቢ በሆነ መንገድ ማግኘት የሚፈልግበት ወቅት በመሆኑ ለዚህ ጠንክሮ መሥራት እንደሚያስፈልግ መናገራቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡

መንግሥትም አቅም ያላቸው ጋዜጠኞች እንዲፈጠሩ የአቅም ግንባታ ሥራ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ ስለመሆኑም አብራርተዋል፡፡ ሚዲያው ዓለም የደረሰበት ደረጃ እንዲደርስ አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግም ገልጸዋል፡፡

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW