አማራጭ ፍትህ የማግኛ መንገዶችን ለማሳደግ ተጨማሪ ስራዎች ማከናወን እንደሚገባ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት መዓዛ አሸናፊ አስታወቁ፡፡
“በኢትዮጵያ የፍትህ ፍላጎቶች እና የመሟላታቸው ሁኔታ” በሚል መሪ ሃሳብ በኢትዮጵያ የወንጀል ፍትህ ስርዓት ላይ በተዘጋጁ ጥናታዊ ሰነዶች ዙሪያ ውይይት እየተካሄደ ነው።
የጥናት ሰነዱ የተዘጋጀው በጠቅላይ አቃቤ ህግ እና “ሂል” በተሰኘ አለም አቀፍ ተቋም ሲሆን በኢትዮጵያ የወንጀል ፍትህ ስርዓት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች እና መፍትሔዎቹን የሚያመላክቱ ናቸው።
የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት መዓዛ አሸናፊ በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር መሠረታዊ የሆኑ የፍትህ ማግኛ ስርዓቶች መኖራቸውን ጠቅሰው፣ ፍርድ ቤት የፍትህ ማግኛ አንደኛው ነው፤ ሁለተኛው ሀይማኖታዊ እንደዚሁም ባህላዊ የፍትህ ማግኛ ስርዓቶች ናቸው ብለዋል።
በኢትዮጵያ የፍትህ ተደራሽነት በበቂ ደረጃ ተሟልቷል መባል አይችልም ያሉት ወ/ሮ መዓዛ አማራጭ ፍትህ የማግኛ መንገዶችን ለማሳደግ ተጨማሪ ስራዎች መከናወን ይገባቸዋል ብለዋል።
የባህላዊና ሀገር በቀል የፍትህ ማግኛ ስርዓቶች በተለያየ ደረጃ አማራጭ ፍትህ የማግኛ መንገዶችን ለማሳደግ ሊሰራ እንደሚገባም ተናግረዋል።
ከዚህ ባሻገር የፍርድ ቤቶችን ተደራሽነት ለማስፋፋት በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን ጠቅሰው በርካታ የዩኒፎርም ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ገልፀዋል።
ፍርድ ቤቶችን በቅርበት ለማያገኙ ተገልጋዮች በአጭር ፅሑፍ ፣ በቪዲዮ ኮንፈረንስ ጉዳዮቻቸውን እንዲከታተሉ እየተደረገ ነው ያሉት ፕሬዝዳንቷ የፌደራል የስራ ቋንቋዎችን ለማይችሉም ጉዳያቸውን በሚችሉት ቋንቋ በትርጉም እንዲከታተሉ ማድረግ መቻሉንም ጠቁመዋል፡፡
ከነዚህ የፍርድ ቤት አገልግሎቶች በተጨማሪ አማራጭ ፍትህ የማግኛ መንገዶችን ለማሳደግ መስራት አስፈላጊ መሆኑንም ወ/ሮ መዓዛ ገልጸዋል፡፡
(በደረሰ አማረ)