አማራ ባንክ በበጎ አድራጎት ስራ ላይ ለተሰማሩ ተቋማት ድጋፍ አደረገ

መጋቢት 23/2015 (ዋልታ) አማራ ባንክ በበጎ አድራጎት ስራ ላይ ለተሰማሩ ስምንት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የገንዘብ ድጋፍ አደረገ፡፡

የባንኩ ዋና ስራ አስፈፃሚ ሄኖክ ከበደ አማራ ባንክ በባንክ ዘርፍ ቀልጣፋ እና የፋይናንስ አገልግሎትን የሚያሳድግ ስራን ከመስራት ባሻገር በማህበራዊ አገልግሎቶች ላይ በስፋት እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡

በዚህም መሰረት በዛሬው እለት ባንኩ ለስምንት የበጎ አድራጎት ተቋማት ያደረገው ድጋፍ ከፋይናንስ ተደራሽነት ባለፈ ሰፊውን ህብረተሰብ ለማገልገል የተቀናጀ ስራን እየሠራ እንደሚገኝ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ባንኩ በቀጣይም ይህን መሰል የማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት እንደሚሰራ ነው የተገለፀው፡፡

በተጨማሪም የመልካምነት እና የቅንነት ወራት በሆኑት በሁለቱ አበይት የሁዳዴ እና የረመዳን አፅዋማት ወቅትን ምክንያት በማድረግ ባንኩ የተለያዩ የበጎነት እንቅስቃሴዎችን እንደሚያካሄድ ተገልጿል፡፡

በሔብሮን ዋልታው