አማቂ ጋዞች ልቀትን በመቀነስ እድገት ለማስመዝገብ ውይይት እየተካሄደ ነው

ሰኔ 14/2014 (ዋልታ) ሙቀት አማቂ ጋዞችን በመቀነስ ምጣኔያዊ ሀብት ማስመዝገብ በሚቻልበት መንገድ ላይ ውይይት እየተደረገ ነው።

ዓለም ዐቀፉ የአረንጓዴ እድገት ኢኒስቲትዩት ባዘጋጀው የውይይት መድረክ የዘርፉ ባለሙያዎች እና በዘርፉ ያሉ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ጌታሁን ጋረደው (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ሙቀት አማቂ ጋዞችን ልቀት በመቀነስ የተረጋጋ ኢኮኖሚ ለመገንባት በትኩረት እየሰራች ነው ብለዋል፡፡

አክለውም በሁሉም ዘርፍ የካርበን ልቀትን መቀነስ የሚቻልበትን መንገድ በፖሊዎች በማካተት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የዓለም ዐቀፉ የአረንጓዴ እድገት ኢኒስቲትዩት የኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር ገመዳ ዳሌ (ዶ/ር) በበኩላቸው ባለፉት 10 ዓመታት ዓለም ዐቀፉ የአረንጓዴ እድገት ኢኒስቲትዩት በኢትዮጵያ ሙቀት አማቂ ጋዞችን ልቀት በመቀነስ እድገት ማስመዝገብ በሚቻልበት መንገድ ላይ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡

ኢኒስቲትዩቱ ሀገራት የረጅም ጊዜ አማቂ ጋዞች ልቀትን በመቀነስ እድገትን ማስመዝገብ በሚችሉበት መንገድ ዙርያ እንደሚሰራም ተጠቁሟል፡፡

የረጅም ዘመን የሙቀት አማቂ ጋዞች ልቀት ቅነሳ ስትራቴጂው የዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ለውጥ ማእቀፋዊ ስምምነት አባል ሀገራት እ.ኤ.አ በፈረንሳይ ፓሪስ የተደረሰውን የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ነው ተብሏል። እቅዱም በ2050 የሙቀት አማቂ ጋዞች ልቀትን ዜሮ ፐርንት ለማድረግ ነው።

በመስከረም ቸርነት