አሜሪካ ለኢትዮጵያ ከ18 ሚሊየን ዶላር በላይ ድጋፍ አደረገች

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ

አሜሪካ በትግራይ ክልል በተካሄደው የህግ የማስከበር ተግባር ለተፈናቀሉ ኢትዮጵያውያን ለሰብዓዊ ድጋፍ የሚውል ከ18 ሚሊየን ዶላር በላይ ድጋፍ ማድረጓን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ አስታውቀዋል፡፡

ድጋፉ በዩኤስጂ አጋሮች የተገኘ ሲሆን፣ ዓለም አቀፍ ሰብአዊ ድርጅቶችን በማገዝ ከኢትዮጵያ ተፈናቅለው በሱዳን የሚገኙ ከ52 ሺህ በላይ ስደተኞችን ፍላጎት ለሟሟላት እና በጅቡቲ እንዲሁም በአፍሪካ ቀንድ ሀገራት የሚገኙ ተፈናቃይ ዜጎችን ለማገዝ ነው ተብሏል፡፡

ኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል፣ በጎርፍ የሚጠቁ ማህበረሰቦችን ለመርዳት እና ከኤርትራ ተፈናቅለው በኢትዮጵያ የሚገኙ ዜጎችን ለማቋቋም የታሰበ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

ድጋፉ መጠለያዎችን፣ አስፈላጊ የጤና እንክብካቤን፣ የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ ዕርዳታን፣ ትምህርትን፣ የአካባቢ ጽዳትና ንፅህና አገልግሎቶችን ለስደተኞች እና ለተፈናቀሉ ዜጎች ለማቅረብ እንደሚውል ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡