አሜሪካ በሩሲያ ላይ አዲስ ማዕቀቦችን ከጣለች ግንኙነታችን ሙሉ በሙሉ ያበቃለታል- ፕሬዝዳንት ፑቲን

ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን

ታኅሣሥ 22/2014 (ዋልታ) “አሜሪካ በሩሲያ ላይ አዲስ ማዕቀቦችን ከጣለች የሁለቱ ሀገራት የሻከረው ግንኙነት ሙሉ ለሙሉ ይቋረጣል” ሲሉ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን አስጠነቀቁ።

የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና የአሜሪካው አቻቸው ጆ ባይደን በወቅታዊ የሩሲያና ዩክሬን ጉዳይ ላይ የስልክ ውይይት አድርገዋል።

ለረጅም ደቂቃዎች የተካሄደው የሁለቱ መሪዎች ውይይት መረጋጋት የታየበት ሆኖም ማስጠንቀቂያዎች የታከሉበት ነበር ተብሏል።

አሜሪካ ማዕቀብ የመጣል ውሳኔ ካላት ትልቁ ስህተቷ እንደሚሆን የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን መናገራቸውን አር ቲን ጠቅሶ ኢዜአ ዘግቧል።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በበኩላቸው ሩሲያ በዩክሬን ላይ ጥቃት የምትከፍት ከሆነ አሜሪካ እና አጋሮቿ ጠንካራ እርምጃ እንደሚወስዱ ገልጸዋል።

ሩሲያና ዩክሬን ከሰሞኑ በድንበር የጸጥታ ስጋት እየተወቃቀሱ መሆናቸው ይታወቃል።

ዩክሬን የሩሲያ 100 ሺሕ የጦር ሠራዊት በምስራቃዊ ድንበር ሰፍሯል፤ ይህ ጥቃት ሊፈፅምብኝ ይችላል የሚል ስጋቷን ገልጻለች።

በአካባቢው ያለውና አሜሪካ ይሁንታ የሚንቀሳቀሰው የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) የጥምር ጦር በሩሲያ ላይ የፀጥታና ደኅንነት ስጋት መደቀኑን ሞስኮ ስትገልፅ ሰነባብታለች።

ፕሬዝዳንት ፑቲን “ኔቶ”ን እና አሜሪካን ባስጠነቀቁበት ንግግራቸው ሩሲያ በግዛታዊ አንድነቷና ሉዓላዊነቷ ላይ የደኅንነት ስጋት እንደማይፈጥር የማረጋገጫ ሰነድ ያስፈልጋታል ብለዋል።

ሆኖም የአሜሪካው አቻቸው ጆ ባይደን የሩሲያ ስጋት እንደሚያሳስባቸው ገልጸው ወደ ስምምነት የሚያስገባ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ እንቸገራለን ማለታቸውን ዘገባው አስታውሷል።