አሜሪካ በቱርክ ላይ ማዕቀብ ጣለች

አሜሪካ የኔቶ አባል በሆነችው ቱርክ ላይ ማዕቀብ መጣሏን አስታወቀች፡፡ ማዕቀቡ ባለፈው አመት ከሩሲያ የገዛችውን ከምድር ወደ አየር ተወንጫፊ ሚሳኤልን ተከትሎ የተጣለ ነው ተብሏል፡፡

እንደ አሜሪካ አገላለጽ ቱርክ የገዛችው መሳሪያ ከሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ቴክኖሎጅ ጋር አብሮ የማይሄድና የማይጣጣም ነው፡፡

ውስብስብ ነው የሚባለውና ዘመናዊው ኤስ 400 ሚሳኤል ለቃል ኪዳኑ ጥምረት አደጋ ነው ስትልም አሜሪካ ገልጻለች፡፡

የአሁኑ ማዕቀብም በቱርክ የጦር መሳሪያ ግዥ እና ተዛማጅ ጉዳዮች ላይ የተጣለ መሆኑን የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት አስታውቋል፡፡

ቱርክ በበኩሏ ማዕቀቡን ተገቢነት የሌለው በማለት አሜሪካ በጉዳዩ ላይ እንድታስብበት ጠይቃለች፡፡

ጉዳዩን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለመፍታት እንደምትሞክርም የሃገሪቱ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ገልጿል፡፡

አሜሪካ ቀደም ብላ ቱርክ ከሩሲያ ከገዛችው የሚሳኤል ሲስተም ጋር ተያይዞ ከኤፍ -35 ተዋጊ አውሮፕላኖች የግዥ ስምምነት ሰርዛታለች፡፡

(ምንጭ፡-ቢቢሲ)