አሜሪካ በኔቶ የምስረታ ጉባኤ ላይ እንዲሳተፉ እስራኤልንና የአረብ አገራትን ጋበዘች

ሰኔ 21/2016 (አዲስ ዋልታ) አሜሪካ በሚቀጥለው ወር በዋሽንግተን ለሚከበረው 75ኛ ዓመት የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) የምስረታ ጉባኤ ላይ እንዲሳተፉ የእስራኤልንና የበርካታ አረብ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችን ጋበዘች።

አሜሪካ በጉባኤው ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ ያደረገችው ለእስራኤል፣ ጆርዳን፣ ኳታር፣ ቱኒዚያ፣ የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች፣ እና ለባህሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች መሆኑን አልጄዚራ ዘግቧል።

ከዚህ በተጨማሪም የጃፓን፣ የደቡብ ኮሪያና የአውስትራሊያን ጨምሮ የ30 አገራት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በ75ኛ የኔቶ ክብረ በዓል ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ ተደርጎላቸዋል ተብሏል።

የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት ዋና ጸሀፊ ለ32 የድርጅቱ አባል አገራት ርዕሰ መንግስታትና ርዕሰ ብሔሮች እንዲ ሳተፉ ጥሪ ማድረጋቸውን ዘገባው አመላክቷል።

የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) በወቅቱ የሶቪዬት ሕብረት ሊቃጣ ይችላል ላሉት አደጋ የጋራ ጸጥታ ለመጠበቅ ሲባል እ.ኤ.አ ሚያዚያ 4 ቀን 1949 ነበር በዋሽንግተን ዲሲ የተመሰረተው።

ስዊድን አዲሷና 32ኛዋ የኔቶ አባል አገር ስትሆን መጋቢት 2024 ነበር ድርጅቱን በይፋ የተቀላቀለችው።