አሜሪካ በአሸባሪው ሕወሓት የተፈፀመው የሰብኣዊ መብት ጥሰት እንዳሳሰባት ገለፀች

ታኅሣሥ 4/2014 (ዋልታ) አሜሪካ የአሸባሪው ሕወሓት ታጣቂዎች በአማራና አፋር ክልል የፈፀሟቸው የሰብኣዊ መብት ጥሰቶች፣ የጭካኔ ድርጊቶችና የሲቪል ተቋማት ውድመት እንዳሳሰባት ገለፀች፡፡

የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ ባወጡት መግለጫ በአማራ እና በአፋር ክልሎች በትግራይ ኃይሎች ተፈጽመዋል የተባሉ ያልተረጋገጡ የሰብኣዊ መብት ጥሰቶች እና የንብረት ውድመቶች በእጅግ አሳሳቢ መሆናቸውን ገልፀዋል።

በዚህም በአማራ እና በአፋር ክልሎች በአሸባሪው ሕወሓት ኃይሎች የተፈጸሙ የሰብኣዊ መብት ጥሰቶችን፣ አስደንጋጭ የጭካኔ ድርጊቶችንና በሕዝብ መሰረተ ልማቶች ላይ የተፈጸሙ ውድመቶችን በተመለከተ እየወጡ ያሉ ሪፖርቶች አሜሪካን አሳስቧታል ብለዋል።

መንግሥት አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በአማራ እና አፋር ክልሎች ወርሮ በያዛቸው አካባቢዎች የፈፀማቸውን ለመናገር የሚከብዱ እጅግ ዘግናኝ የሰብኣዊ መብት ጥሰቶች፣ የጅምላ ጭፍጨፋዎች እና የንብረት ዘረፋና ወድመቶች ዓለም ዐቀፍ ተቋማት በአካል ተገኝተው እንዲመለከቱ ጥሪ ማድረጉ ይታወቃል።

አሸባሪው ሕወሓት የፈፀማቸውን የሰብኣዊ መብት ጥሰቶች፣ የጅምላ ጭፍጨፋዎች እና የሲቪል መሰረተ ልማቶች ውድመት በይፋ ለማውገዝ ዳተኛ ሆና የቆየችው አሜሪካ ድርጊቱን እንድታወግዝ በአገር ቤት እና በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች በተለያየ መንገድ ግፊት እያደረጉ ይገኛል።