አምባሳደር ሙክታር ከድር በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት አማራጮች ዙሪያ ገለጻ አደረጉ

መስከረም 7/2015 (ዋልታ) ለአራተኛ ጊዜ በተካሄደው የምስራቅ ካፕ የውጭ ንግድ ሲፖዚየም ላይ በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር አምባሳደር ሙክታር ከድር (ፒኤችዲ) የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት ዕድሎችና ማበረታቻዎችን አስተዋውቀዋል።

አምባሳደሩ በሲምፖዚየሙ ላይ ባደረጉት ንግግር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያ እያካሄደች ባለችው ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ ሪፎርም ከመቼውም ጊዜ በላይ ለውጭ ለባለሃብቶች ምቹ የኢንቨስትመንት መዳረሻ እንደሆነች አስረድተዋል።

በተለይም መንግስት ትኩረት በሰጣቸው የኢነርጂ፣ ማዕድን፣ በግብርና ማምረቻ፣ ጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት፣ ቱሪዝም፣ ቆዳ እና የቆዳ ውጤቶች እንዲሁም ፋርማሲውቲካል የኢንቨስትመንት መስኮች የተሻሻሉ የኢንቨስትመንት ህጎች እንዲሁም አመቺ መሰረተ-ልማት ዝርጋታዎችና ማበረታቻዎች በሰፊው አብራርተዋል ።

ሲምፖዚየሙ ዓለም -አቀፉ ንግድ ላይ እየታዩ ያሉትን ተግዳሮቶች ለመመከት እንዲቻል አዳዲስ ስትራቴጂዎችን ለመቀየስ ያለመ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት መረጃ ጠቁሟል።