አምባሳደር ስለሺ በቀለ በዋሽንግተን ዲሲ የኢትዮጵያን ድምጽ ላሰሙ ዳያስፖራዎች አድናቆታቸውን ገለጹ

ጳጉሜ 2/2014 (ዋልታ) በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ስለሺ በቀለ በዋሽንግተን ዲሲ የኢትዮጵያን ድምጽ ለማሰማት ሰላማዊ ሰልፍ ላደረጉ የዳያስፖራ አባላት አድናቆታቸውን ገለጹ።

በዋሽንግተን ዲሲ ዙሪያ ካሉና ከሌሎች ግዛቶች በመሰባሰብ በኢትዮጵያ ላይ የሚደረገውን ጫናና የመገናኛ ብዙሃን ዘመቻ በመቃወም በሰላማዊ መንገድ የተቃውሞ ድምጻቸውን ላሰሙ የዳያስፖራ አባላት ትልቅ አድናቆት ማቅረባቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመልክቷል።

ትናንት ማምሻውን በአሜሪካ ዋሺንግተን ዲሲ አሸባሪው ሕወሓት ዳግም የከፈተውን ጦርነት የሚያወግዝ ሰላማዊ ሰልፍ ተካሂዷል።

ሰልፉ “በአገር ሕልውናና አንድነት አንደራደርም!” በሚል መሪ ሀሳብ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ፊት ለፊት ተከናውኗል።

የሰላምና አንድነት ለኢትዮጵያ ግብረ ኃይል ሰልፉን ከአገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ጋር በትብብር እንዳዘጋጀውም ተገልጿል።