አምባሳደር ስለሺ በቀለ ከአሜሪካ የሴኔት ደህንነት ጉዳዮች ሰብሳቢ ማርክ ዋርነር ጋር ተወያዩ

መስከረም 19/2015 (ዋልታ) በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ስለሺ በቀለ በወቅታዊ ሁኔታዎች ዙርያ ከአሜሪካ የሴኔት የደህንነት ጉዳዮች ሰብሳቢ ማርክ ዋርነር ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም በኢትዮጵያ ስላለው ግጭት፣ የኢትዮጵያና አሜሪካ የሁለትዮሽ ግንኙነት እና በልማቱ ዘርፍ ዳያስፖራው ያለውን ሚና በተመለከተ ማንሳታቸውን ገልጸዋል።

ሴናተር ማርክ ዋርነር ከ2008 ጀምሮ በሴናተርነት በማገልገል ላይ ሲሆኑ ከጥር 2021 አንስቶ የሴኔቱ የደህንነት ጉዳዮች ኮሚቴ ሰብሳቢ ሆነው በመስራት ላይ ናቸው።

በተያያዘ ዜና አምባሳደር ስለሺ በአገሪቷ ከሚኖሩ ከ200 በላይ ዲያስፖራዎች ጋር ውጤታማና ጠቃሚ ውይይት ማድረጋቸውን አመልክተዋል።

ውይይቱ ዲያስፖራው የኢትዮጵያና አሜሪካ ግንኙነትን በማጠናከር፣ ኢትዮጵያን በመደገፍና በልማት ስራዎች እየተወጣ ያለውን ሚና በተመለከተ እንደሆነ ተናግረዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡

 

አምባሳደር ስለሺ በአሜሪካ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ለአገራቸው እያደረጉት ላለው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበው አሁንም አጋርነታቸውን እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቅርበዋል።