ሐምሌ 07/2013 (ዋልታ) – በጂቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ በጂቡቲ ከአሜሪካ አምባሳደር ጆናታን ፕራት ጋር ተወያይተዋል፡፡
አምባሳደር ብርሃኑ በውይይታቸው ወቅት ህወሃት አካባቢውን ወደ ሰላም ለማምጣት በሚደረገው ጥረት ላይ እክል እየፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በትግራይ ክልል የተደረሰውን የተናጥል የተኩስ አቁም በማስታወስ፣ መንግስት አርሶ አደሩ የክረምቱን ወቅት በተረጋጋ ሁኔታ እንዲጠቀም በማሰብ ሰራዊቱን ከትግራይ ክልል ማስወጣቱንም ለአምባሳደሩ ገልጸውላቸዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም መንግስት የኤርትራን ወታደር ከኢትዮጵያ ድንበር ማስወጣቱን በመጥቀስ፣ መንግስት በትግራይ ክልል ሰብአዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች ድጋፍ ለማድረስ እየሰራ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
ይሁን እንጅ ህወሃት ከዚህ በተቃራኒው አሁንም የሚፈጽመውን ጭካኔ የተሞላበት ግድያ እንደቀጠለበትና አካባቢውን ወደ ሰላም ለማምጣት በሚደረገው ጥረት ላይ እንቅፋት እየፈጠረ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
አምባሳደር ብርሃኑ አያይዘውም ባለፈው ሰኔ 14 ቀን የተካሄደው 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ግልጽና ታማኝነት ባለው መልኩ መካሄዱን ጠቁመዋል፡፡
የሚዲያ ተቋማት ሲቪክ ማህበራት፣ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን እና ፍርድ ቤቶችም የምርጫውን ሂደት መታዘባቸውን አንስተዋል፡፡
የአሜሪካው አምባሳደር ጆናታን ፕራት በበበኩላቸው፣ ምርጫው በተሳካ ሁኔታ በመካሄዱ እንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈው የኢትዮ ጂቡቲን የሁለትዮሽ ግንኙነት አድንቀዋል፡፡
አምባሳደሮቹ በውይይታቸው ወቅት በሁለቱ ሀገራት የጋራ ጉዳዮች በሆኑ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን ከጂቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡