አምባሳደር ተፈሪ መንግሥት በሠላምና ልማት ላይ እየተገበራቸው ያሉ ሥራዎችን ለእንግሊዝ ፓርላማ አባላት አብራሩ

ሰኔ 15/2014 (ዋልታ) በእንግሊዝ የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈሪ መለሰ መንግሥት በሀገሪቱ ዘላቂ ሠላም ለማስፈንና ልማትን ለማረጋገጥ እየወሰዳቸው ያሉ እርምጃዎችን በኢትዮጵያና ጂቡቲ ጉዳይ ላይ ለተቋቋመው የእንግዚዝ የፓርላማ አባላት አብራርተዋል፡፡

ሕወሓት ለሦስተኛ ዙር ወታደራዊ ጥቃት እየተዘጋጀ መሆኑንም ለፓርላማ አባላቱ ያስረዱት አምባሳደር ተፈሪ ድርጊቱ ሊኮነን እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

ሕወሓት ጥቃቱን ለመፈጸም የተዘጋጀው ታዳጊ ሕጻናትን በግድ በመመልመል ጭምር መሆኑን ያስገነዘቡት አምባሳደሩ ጉዳዩን ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሊያወግዘው እንደሚገባው አስምረውበታል፡፡

ኢትዮጵያ የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ በምግብ ራሷን ለመቻል ጥረት እያደረገች መሆኑን ለፓርላማ አባላቱ ያስረዱት አምባሳደሩ በአፍሪካ ቀንድ የተከሰተው የአየር ንብረት ለውጥ በአንዳንድ የኢትዮጵያ ክፍሎች ድርቅ ማስከተሉን ጠቁመዋል፡፡

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ኢትዮጵያንና የቀጣናውን ሀገራት ለገጠማቸው ሰብዓዊ ቀውስ ድጋፍ እንዲያደርጉ አምባሳደር ተፈሪ አጽንኦት ሠጥተው ጠይቀዋል።

የፓርላማ አባላቱ በበኩላቸው በኢትዮጵያ እየተስተዋለ ያለውን ፖለቲካዊ መሻሻልና ሀገሪቷ የያዘችውን በምግብ እህል ራስን የመቻል መርኃ ግብር ማድነቃቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

የፓርላማ አባላቱ ኢትዮጵያን መደገፋቸውን እንደሚቀጥሉ እና የእንግሊዝ ባለሃብቶችም በኢትዮጵያ መዋዕለ-ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ለማስቻል መረጃ እንደሚሰጡም ቃል ገብተዋል፡፡

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW