አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ የተባበሩት መንግሥታትን ሚዛን የሳተ ወቀሳ ተቹ

ኅዳር 30/2014 (ዋልታ) አሸባሪው ሕወሓት እርዳታ ጭነው ትግራይ የገቡ 1 ሺሕ 10 ተሽከርካሪዎችን ጠልፎ ለጦርነቱ ሲጠቀም የተስማማ በሚመስል መልኩ ዝምታን የመረጠው የተባበሩት መንግሥታት የኢትዮጵያ ወታደሮች 3 ተሽከርካሪዎቼን መጠቀማቸውን አወግዛለሁ ሲል መደመጡ ተገቢነት እንደሌለው በመንግሥታቱ ኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ተቹ፡፡

አምባሳደር ታዬ የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ ቃል አቀባይ የሰጠውን የዓለም ምግብ ፕሮግራም እንቅስቃሴ የተመለከተ መግለጫ ጠቅሰው ባስተላለፉት መልዕክት የኢትዮጵያ ወታደሮች 3 የመንግሥታቱን ተሽከርካሪዎችን አዘዋል በሚል ለተሰማው ያልተረጋገጠ ወሬ ፈጥኖ የውግዘት መግለጫን ላወጣው የተባበሩት መንግሥታት የሽብር ቡድኑ 1 ሺሕ 10 ተሽከርካሪዎችን ጠልፎ እስካሁንም በይፋ ሲጠቀምባቸው ምንም ያላለ ድርጅት መሆኑን አስታውሰውታል፡፡

አሸባሪው ቡድን በኮምቦልቻና በተለያዩ አካባቢዎች የእርዳታ መጋዘኖችን ጨምሮ የተለያዩ ንብረቶችን ሆን ብሎ ሲወድምና ሲዘርፍ እንደነበር አስምረዋል፡፡

ይሁን እንጅ አሸባሪው ከዘረፈ በኋላ ለቀጣይ የፕሮፖጋንዳ ሥራው የአካባቢውን ነዋሪዎች በመሰብሰብና ወደ መጋዘኖች በማስገባት እነሱ እንደዘረፉ በማስመሰል ቀረጻ ያደርግ እንደነበርም የዓይን እማኞች ለዋልታ ሲገልጹ ሰንብተዋል፡፡

እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ የተባበሩት መንግሥታት ቃል አቀባይ ወረራና ጥቃት ከፈፀመው የሽብር ቡድኑ ሕወሓት ይልቅ የአካባቢውን ማኅበረሰብ መውቀሱ የጥቃት ሰለባዎችን ወንጀለኛ እንደማድረግ ይቆጠራል ሲሉ ነው የመንግሥታቱን ቃል አቀባይ በቲውተር አድራሻው በጠቀሱበት መልዕክታቸው የተቹት፡፡