አምባሳደር ነቢል ማህዲ ከደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዝዳንት ጋር ተወያዩ

አምባሳደር ነቢል ማህዲ

ግንቦት 29/2013 (ዋልታ) – በደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ነቢል ማህዲ ከደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዝዳንት ሬቤካ ኒያንዴንግ ዲማቢዮር ጋር በሁለትዮሽና አካባቢያዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።

በውይይቱ አምባሳደር ነቢል የሕዳሴ ግድብ ድርድር ሂደት፣ የኢትዮ-ሱዳን የድንበር ሁኔታ እንዲሁም የትግራይ ወቅታዊ ሁኔታና በቀጣዩ አገራዊ ምርጫ ዙሪያ ለምክትል ፕሬዝዳንቷ ገለጻ አድርገዋል።

ምክትል ፕሬዝዳንቷ በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ለደቡብ ሱዳን ዘመን የማይሽረው ውለታ መዋላቸውን አንስተው፣ በዚህም ደቡብ ሱዳን የሕዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅ ከኢትዮጵያ ጋር የሚያዋስኗትን ሦስት ክልሎች ተጠቃሚ ለማድረግ ዕቅድ መኖሩን ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል ያለው የድንበር ውዝግብም በውይይት መፍታት የሚገባው መሆኑን ገልጸው፣ ደቡብ ሱዳን ችግሩ በውይይት እንዲፈታ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን አረጋግጠዋል።

ከዚህ ባሻገር በትግራይ ያለው ሁኔታ በቅርቡ ሙሉ ለሙሉ ተስተካክሎ በኢትዮጵያ ዘላቂ መረጋጋት እንደሚመጣ ተስፋ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ምርጫ ለማከናወን የሚያስችል ልምድና ተሞክሮ እንዳላት በማስታወስ፣ ቀጣዩም አገራዊ ምርጫ በተሳካ ሁኔታ እንደሚጠናቀቅ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

በመጨረሻም የደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነት አፈጻጸም የዘገየ ቢሆንም በትክክለኛው መንገድ ላይ መሆኑን አረጋግጠው ኢትዮጵያም ለሂደቱ እያደረገች ያለውን ድጋፍ አጠናክራ እንድትቀጥል መጠየቃቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።