አምባሳደር ነቢል ማህዲ ከደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዝዳንት ጋር ተወያዩ

ሰኔ 16/2013(ዋልታ) – አምባሳደር ነቢል ማህዲ ከደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ጄምስ ዋኒ ኢጋ ጋር በወቅታዊ  ሁኔታ  ዙሪያ  ተወያይተዋል።

አምባሳደር ነቢል የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ረጅም ታሪክ ያስቆጠረና በጠንካራ መሠረት ላይ የተገነባ መሆኑን በማውሳት፤ ይህንንም የሁለቱን ሀገራት ሕዝቦች ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተጨባጭ የልማት ሥራዎች መደገፍ እንደሚገባ ገልጸዋል።

ከዚህ አንጻር ሁለቱን ሀገራት በመንገድና በኤሌክትሪክ ኃይል መሠረተ-ልማት ለማስተሳሰር የተጀመረው ጥረት እንዲሳካ ርብርብ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

ከዚህ ባሻገር ኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ-ግብር በጎረቤት ሀገራት ጭምር ለማስጀመር የያዘችውን ዕቅድ ለምክትል ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል።

በዚሁ መሠረት የፊታችን ሐምሌ 2 ከሚከበረው የደቡብ ሱዳን 10ኛ ዓመት የነጻነት በዓል ጎን ለጎን ችግኝ ተከላው አንድ አካል እንዲሆን ፍላጎት መኖሩን ተናግረዋል።

ምክትል ፕሬዝዳንቱም የዕቅዱን ጠቀሜታና ወቅታዊነት በመግለጽ ለተግባራዊነቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጻዋል።

በተጨማሪ አምባሳደር ነቢል በሕዳሴ ግድብ ድርድር ሂደት፣ በኢትዮ-ሱዳን የድንበር ውዝግብ አስመልከቶ ገለጻ አድርገዋል።

እንዲሁም 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን ያሸነፉበት ነጻና ሰላማዊና ምርጫ ሆኖ መጠናቀቁን ለምክትል ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል።

ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ዋኒ ኢጋ ኢትዮጵያዊያን ለደቡብ ሱዳን ነጻነት ከደቡብ ሱዳናዊያን ጎን የሕይወት መስዕዋትነት መክፈላቸውን በማስታወስ፣ ይህ ውለታ ሁሌም የማይዘነጋ መሆኑን ገልጸዋል።