አምባሳደር ነቢል ማህዲ ከደቡብ ሱዳን የውሃ ሃብትና መስኖ ሚንስትር ጋር ተወያዩ

መጋቢት 24/2013 (ዋልታ) – በደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ነቢል ማህዲ ከደቡብ ሱዳን የውሃ ሃብትና መስኖ ሚንስትር ከማናዋ ፒተር ጋትኩት ጋር ውይይት አድርገዋል።

አምባሳደር ነቢል በውይይቱ ወቅት ደቡብ ሱዳንና ኢትዮጵያ ጠንካራ ወዳጅነት ያላቸው መሆኑን በማስታወስ በቀጣይ በኢኮኖሚና በልማት መስኮች የበለጠ ማስተሳሰር ተገቢ መሆኑን ለሚኒስትሩ ገልጸውላቸዋል።

በተጨማሪም የህዳሴ ግድብ ያለበትን ሁኔታ በተመለከተ ገለጻ በማድረግ፣ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ከኢትዮጵያ አልፎ ለጎረቤት ሃገራት በጎ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አብራርተዋል።

ከግድቡ ጋር ተያይዞ ከታችኞቹ የተፋሰስ ሃገራት ጋር ያለው ልዩነት በአፍሪካ ኀብረት ማዕቀፍ በሦስትዮሽ ድርድር እንዲፈታ ኢትዮጵያ ያላትን አቋምም አስረድተዋል።

በተያያዘም የናይል ተፋሰስ ሃገራት የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ደቡብ ሱዳንን ጨምሮ ለተፋሰሱ ሃገራት ጠቃሚ መሆኑን ገልጸዋል።

ሚኒስትሩ ማናዋ ፒተር በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳን ያበረከተችው አስተዋጽኦ ታላቅ መሆኑንና እስካሁንም በተለያዩ መስኮች ጠንካራ ድጋፍ እያደረገች መሆኑን በማውሳት አመስግነዋል።

የህዳሴ ግድብን በተመለከተ መንግሥታቸው ኢትዮጵያ ሃብቷን የማልማት ሙሉ መብት እንዳላት እንደሚያምን እንዲሁም ከታችኛው የተፋሰሱ ሃገራት ጋር ያለው ልዩነት በድርድር መፍታት እንደሚገባ ገልጸዋል።

የናይል ተፋሰስ ሃገራት የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት በተመለከተ የሃገሪቱ ፓርላማ በቅርቡ ሲከፈት እንደሚጸድቅ ሚኒስትሩ ማረጋገጣቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።