አምባሳደር ነብያት ለአፍሪፖል በወቅታዊ ሁኔታዎች ዙሪያ ገለጻ ሰጡ

በአልጄሪያ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ነብያት ጌታቸው መቀመጫውን በአልጀርስ ላደረገው የአፍሪካ ኀብረት የፖሊስ ተቋማት ትብብር ማዕቀፍ AFRIPOL ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ጣሪቅ ሸሪፍ በኢትዮጵያ በትግራይ ክልል የተካሄደውን የህግ ማስከበር ሥራና የሰብዓዊ ዕርዳታ እንቅስቃሴ እንዲሁም በኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር ግጭትና ኀዳሴ ግድብ ድርድርን በተመለከተ ገለፃ አድርገዋል፡፡

አምባሳደር ነብያት ከዶ/ር ጣሪቅ ሸሪፍ ጋር ባደረጉት ውይይት የፌዴራል መንግሥት በትግራይ ክልል ያደረገው የህግ ማስከበር ዘመቻ መጠናቀቁንና በክልሉ የሰብዓዊ ዕርዳታ በመንግስትና በተለያዩ ዓለም ዓቀፍ ተቋማት ትብብር ለማድረስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ስደተኞችን በማስተናገድ ረገድ በቅርቡ የተባበሩት መንግስታ ድርጅት የስደተኞች ኮሚሽነር በስፍራው ተገኝተው ጉብኝት ማድረጋቸውንና በቀጣይ ሥራዎች ዙሪያ ከመንግሥት ኃላፊዎች ጋር ውይይት መክረዋል፡፡

በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል የተከሰተው የድንበር ግጭትም ታሪካዊ ዳራውን በመግለጽ ኢትዮጵያ ሱዳን ወደ ቀድሞዋ ሥፍራ ተመልሳ ድርድሩ መካሄድ እንዳለበትና ችግሩ ሊፈታ የሚችለውም በውይይት ብቻ መሆኑን እንደምታምን ገልጸዋል፡፡

ዶ/ር ሸሪፍ በበኩላቸው በአፍሪካ  ግጭቶች እንዳይበራከቱ ተቋማቸው ህግ ማስከበር ዙሪያ ከአባል ሃገራት ጋር የትብብርና የአቅም ግንባታ ሥራዎች እንደሚሰሩ በመግለፅ፤ ድንበር ዘለል ግጭቶች እንዳይባባሱ በውይይት መፍታት አስፈላጊ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

አፍሪፖል በአፍሪካ ኀብረት በአባል ሃገራት የፖሊስ ተቋማት መካከል ሁለንተናዊ ትብብር ለማድረግ የተቋቋመ አካል ሲሆን፤ ተቀማጭነቱም አልጄሪያ፣ አልጀርስ ከተማ መሆኑን ከውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡