አምባሳደር ጀማል በከር ከባህሬን የነዳጅ ሚኒስትር ጋር በሁለትዮሽና ቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያዩ

ታኅሣሥ 7/2014 (ዋልታ) በባህሬን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ቆንስላ ጽህፈት ቤት መሪ አምባሳደር ጀማል በከር ከባህሬን የነዳጅ ሚኒስትር ሼክ መሀመድ ጋር በሁለትዮሽ፣ ቀጣናዊ እንዲሁም ባለብዙ ወገን ግንኙነቶች በሚጠናከሩበት ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርገዋል፡፡
አምባሳደር ጀማል በውይይታቸው ወቅት በኢትዮጵያ ያለውን አጠቃላይ የሰላምና የጸጥታ፣ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የኢንቨስትመንት ሁኔታዎች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ሼክ መሀመድ በበኩላቸው ለተደረገላቸው ገለጻ አመስግነው ኢትዮጵያ ቀደምት የስልጣኔና የነጻነት ሀገር መሆኗን ጠቁመው ዘርፈ ብዙ እድሎች እንዳላትም አንስተዋል፡፡
በሌላ በኩል አገራቸው በብረት ማዕድን፣ ኮባልትና በአልሙኒዬም ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት እንዳላት አመላክተዋል፡፡
ሁለቱ ኃላፊዎች የሀገራቱን የሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን ግንኙነቶችን የበለጠ እንዲጠናከር በጋራ ለመስራት ከመግባባት ላይ መድረሳቸውን ከውወጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡