አስተማማኝ የዲጂታል ፋይናንስ ሥርዓት ለመገንባት በትኩረት እየተሠራ ነው – ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ


መጋቢት 17/2016 (አዲስ ዋልታ) አስተማማኝ የዲጂታል ፋይናንስ ሥርዓት ለመገንባት በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ያለመ የፓናል ውይይት ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት እና የተቋማት የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት ተካሂዷል።

በመድረኩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንደገለጹት ከዲጂታል ስርዓቱ መገኘት የነበረበት ትርፍ እየተገኘ ባለመሆኑ የፈጠራ ባለሙያዎች በተዘረጋው ፕላትፎርም መሳተፍ እና ሀብት ማግኘት አለባቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዲጂታል ዘርፉ ያለው ስኬት አንጻራዊ እንጂ ገና ብዙ ይቀረናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምኅረቱ በበኩላቸው የፋይናንስ ዓላማ የኅብረተሰቡን ቁጠባ ወደ ኢንቨስትመንት መቀየር መሆኑን ገልጸው የዲጂታል ፋይናንስ ሥርዓቱ መዘመን እና የመሠረተ ልማት ግንባታ እየተሻሻለ የመጣውን የክፍያ ሥርዓት የሚያቀላጥፍ ነው ብለዋል።

በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ በርካታ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት አሰራራቸው ማኑዋል በመሆኑ ጊዜ እና ጉልበት በከንቱ እየባከነ እንደሆነም አንስተዋል።

ይህንንም ለመቅረፍና የሚስተዋለውን ተግዳሮት ለመቀነስ በዘርፉ የሚሰራውን ስራ በማጠናከር ላይ እንገኛለን ብለዋል።

ባለፈው በጀት ዓመት በዲጂታል የክፍያ ሥርዓት ከ5 ትሪሊዮን ብር በላይ ክፍያ መፈጸሙንና በተያዘው ዓመትም እስካሁን ከ4 ትሪሊዮን ብር በላይ ክፍያ መከናወኑን ገልጸዋል።

ከውስጥና ከውጭ የሚቃጣውን ጥቃት ለመመከት ሳምንቱን በሙሉ ለ24 ሰዓታት እየተሠራ እንደሆነ የገለጹት ደግሞ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሃሚድ ናቸው።

በዐምደወርቅ ሽባባው