ሐምሌ 13/2013 (ዋልታ) – ጊዜውን ጠብቆ መክሰሙ በማይቀረው አሸባሪ የህወሃት ቡድን ላይ ተገቢውን እርምጃ በመውሰድ ሃገርን ለማሻገር በተጠናከረ አንድነት መስራት ይገባል ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ።
ርዕስ መስተዳድሩ ህዝቡ በጎንደር ግንባር ለሰራዊቱ እያደረገ ያለውን የደጀንነት ተሳትፎ በአካል በመገኘት ከጎበኙ በኋላ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ነው ሀሳባቸውን የገለጹት፡፡
በመግለጫቸው አቶ ሽመልስ ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያዊነትን በማስቀደም እንደ ትውልድ የተጣለብንን ሃላፊነት በመወጣት ሃገራችንን ወደ ፊት ለማሻገር በአንድነት የተጠናከረ ትግል ማድረግ ይኖርብናል ብለዋል።
“የኦሮሚያ ክልል ህዝብና መንግስት በኢትዮጵያ አደጋ የሚሆኑ ጉዳዮችን ለመቅረፍ ከወንድም ህዝቦች ጋር አስፈላጊውን መስዋእትነት ለመክፈል ዝግጁ ነው” ያሉት አቶ ሽመልስ የሃገርን አንድነት ለማስጠበቅ መስዋዕትነት መክፈል ከአባቶች ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ አኩሪ ታሪክ መሆኑን አስረድተዋል።
“በፖለቲካ የተሸነፈውና ምንም የፖለቲካ አቅም የሌለው አሸባሪ የህወሃት ቡድን ላለፉት አርባ አመታት ከሽፍትነት እስከ መንግስት፤ ከመንግስትነት ደግሞ ተመልሶ ወደ ሽፍትነት የወረደ ነው” ብለዋል፡፡
“ኢትዮጵያ የቆየችው በመስዋእትነት በመሆኑ ዛሬም ይሕን መስዋእትነት ከፍለን የኢትዮጵያን አንድነት እናስቀጥላለን” ያሉት አቶ ሽመልስ “የጠላትን አሉባልታና ፕሮፓጋንዳ ትተን በአንድነታችን ጉዳይ ላይ አጠናክረን መስራት ይገባናል” ሲሉ ተናግረዋል።
ህወሃት ላይ ዳግም ነፍስ ሊዘሩበት የሚፍጨረጨሩ ሃይሎች ከቶም አይሳካላቸውም ያሉት አቶ ሽመልስ “ኢትዮጵያ በልጆቿ መስዋእትነት አንድነቷ ተጠብቆ በድሎችዋ ታጅባ ወደፊት ትቀጥላለች” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
“ወቅቱ እንደሚጠይቀን ሁለት ነገሮች በአንድ እጃችን ልማታችንን በሌላኛው እጃችን ደግሞ ሰላማችንን በማስጠበቅ የኢትዮጵያን አንድነትና ብልጽግና በመስዋእትነት እናረጋግጣለን” ብለዋል፡፡.
“አሸባሪው የህወሃት ቡድን የከፈተብን ጦርነት በኢትዮጵያ አንድነት ላይ የተቃጣ ጥቃት በመሆኑ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ከዳር አስከ ዳር በመነቃነቅ በጋራ ልንመክተው ይገባል” ሲሉም አክለዋል፡፡
የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ጄኔራል ተመስገን ጥሩነህ በበኩላቸው “የህወሃት የከፈተው ጦርነት በአማራ ክልል ለይ ብቻ ሳይሆን በመላ ኢትዮጵያ ላይ የተቃጣ ጥቃት ነው” ብለዋል፡፡
“ይህን ጦርነት የአማራ ክልል ብቻ አድርጎ የሚወስደው ሃይል ካለ እሱ የሽብር ቡድኑ ብቻ ነው” ያሉት አቶ ተመስገን ዘመቻው የህልውና ዘመቻ እንደመሆኑ ሁሉም ክልሎች እያደረጉት ያለውን ተሳትፎና ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በጎንደር ግንባር የህዝቡን የደጀንነት ተሳትፎና የሰራዊቱ የግዳጅ አፈጻጸም ዝግጁነት እጅግ የሚያኮራ መሆኑንን ማረጋገጣቸውንም ገልጸዋል።
እንደ ኢዜአ ዘገባ “ሀገር ለማፍረስ ሌት ተቀን የሚሯሯጠውን የሸብር ቡድን ግብአተ መሬት ለማፋጠን ኢትጵያውያን ዛሬም እንደትናንቱ በህብረትና በአንድነት እንቁም” ሲሉም ዳሬክተር ጄነራሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።