አሸባሪው ህወሃት በሀገሪቱ ላይ የደህንነት ስጋት ሆኖ እንዳይቀጥል ሆኖ ተደምስሷል- ሌ/ጄ ባጫ ደበሌ

             ሌ/ጄ ባጫ ደበሌ

ሰኔ 25/2013 (ዋልታ) – አሸባሪው ህወሃት በሀገሪቱ ላይ የደህንነት ስጋት ሆኖ እንዳይቀጥል ሙሉ ለሙሉ መደምሰሱን የመከላከያ የሰራዊት ግንባታ ስራዎች ዋና አስተባባሪ ሌተናል ጄነራል ባጫ ደበሌ ገለፁ፡፡

ዋና አስተባባሪው ሌተናል ጄነራል ባጫ ደበሌ ከክፍሉ ከፍተኛ መኮንኖች ጋር ባደረጉት ውይይት፣ ጁንታው ከሰሜን ዕዝ የዘረፋቸውን የሀገር መጠበቂያ ትጥቆች ይዞ ለመዋጋት ቢሞክርም በሰራዊታችን ጀግንነትና አይበገሬነት በሶስት ሳምንት ውስጥ የመደበኛ ውጊያ መዋጋት እንዳይችል አድርጎ ደምስሶታል ብለዋል፡፡

በመደበኛ ውጊያ ተመቶ የተበታተነው የጁንታው ሃይል በሽምቅ ውግያ ለመዋጋት ቢሞክርም ሰራዊታችን የጁንታውን አውራ አመራሮችና ተዋጊዎቹን ከተደበቁበት ዋሻና ጎሬ እየለቃቀመ በመደምሰስ እና ለህግ በማቅረብ የፈፀመው ግዳጅ የተሳካ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

የመከላከያ ሰራዊታችን የጁንታው ቡድን በመደበኛም ይሁን በሽምቅ የመዋጋት አቅም እንዳይኖረው አድረጎ በመደምሰሱ የጥፋት ሃይሉ አማራጭ ያደረገው የውሸት ፕሮፖጋንዳ በመስራት ህዝቡ ውስጥ ገብቶ ህፃናትንና አዛውንትን ከፊት አስቀድሞ መዋጋትን መርጧል ብለዋል፡፡

ሰራዊታችን በትግራይ ክልል ህግን ለማስከበር 8 ወር ሲቆይ ህዝቡ የሰላም ተጠቃሚ እንዲሆንና ሰብአዊ አገልግሎቶችና ድጋፎች ለህዝብ እንዲደርሱ መስዋዕትነትን በመክፈል ጭምር ያገለገለ ቢሆንም፣ ከህዝቡ የተሰጠው ምላሽ ግን በተቃራኒው ሆኗል ነው ያሉት፡፡

የህዝቡን ፍላጎት ለማሟላትና የጥሞና ግዜ ለመስጠት መንግስት በወሰነው ውሳኔ መሰረት ሰራዊቱ መቀሌን ለቆ ሲወጣ በህዝብ መሃል ተደብቆ የነበረው የጁንታው ሃይል መሃል ከተማ ወጥቶ ጨፈረ እንጂ ከሰራዊታችን ጋር አልተዋጋም የመወጋትም አቅም እንደሌለው መግለጻቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡