ነሐሴ 11/2013 (ዋልታ) – አሸባሪው ህወሃት ከሀገራችን ተወግዶ የሠላም አየር እስከሚረጋገጥ ድረስ የሲዳማ ህዝብና መንግሥት እረፍት የለንውም አሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ።
ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ዙሪያ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ አሸባሪው ህወሓት በ27 ዓመታት የስልጣን ቆይታው ሀገሪቱን በከፍተኛ ሁኔታ ሲበዘብዝና የህግ የበላይነትን በመጣስ ህዝብን ሲበድልና ሲጨቁን መቆየቱን አስታውሰዋል።
በዚህ የተማረረው የሀገሪቱ ዜጋ ከዳር ዳር በመነቃነቅ አሸባሪውን ቡድን ከጫንቃው ላይ አሽቀንጥሮ ቢጥለውም ተመልሶ ሀገሪቱን ለመበዝበዝና ለማጥፋት እየተፍጨረጨረ እንደሚገኝ ነው ያመለከቱት።
የአሸባሪውን ህወሃት መራራነት የቀመሰው የሲዳማ ህዝብ የቡድኑን የጥፋት ተልዕኮ ተቀናጅቶ መግታት እንዳለበት አምኖ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
በአሁኑ ወቅት የክልሉ ልዩ ኃይል ፖሊስ አባላት በተሰጣቸው ግዳጅ ግንባር ላይ እየተፋለሙ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ “4 ሺህ የሚጠጉ የክልሉ ወጣቶችም በፍቃደኝነት ለመዝመት ወታደራዊ ስልጠና እየተከታተሉ ነው ማለታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።