አሸባሪው ህወሓትን ለማጥፋት የሚደረገው ትግል በአሸባሪው ሸኔ ላይም ተግባራዊ ሊደረግ ይገባል – አቶ ታዬ ደንደአ

ነሃሴ 7/2013 (ዋልታ) – አሸባሪው ህወሓትን ለማጥፋት የሚደረገው ትግል በአሸባሪው ሸኔ ላይም በተመሳሳይ መልኩ ሊተገበር ይገባዋል ሲሉ የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት የሕዝብ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ታዬ ደንደአ  ገልጸዋል፡፡

አቶ ታዬ ደንደአ  አሸባሪው ህወሓትም ሆነ ሸኔ ለሀገር እና ለህዝብ ጠንቅ  ናቸውም ነው ያሉት።

የኦሮሞ ሕዝብ ከሌሎቹ ወንድሞቹ ጋር በመሆን ኢትዮጵያን ለመጠበቅ፣ ሉዓላዊነቷን ለማስከበር፣ ብልጽግናዋን እውን ለማድረግ መረባረብ ይገባዋል ብለዋል፡፡

የቡድኖቹ በጋራ ለመንቀሳቀስ መስማማት በግልጽ አብረን ስንሰራ ነበር፣ ኦሮሞን ስናሰቃይ፣ ኢትዮጵያ ላይ ወንጀል ስንፈጽም የነበረው በጋራ ነው፣ ወንጀሎቹ ሁለታችንንም እኩል ይመለከቱናል የሚል መልዕክት አለው ሲሉ ተናግረዋል።

በመሆኑም ሕዝቡ ሸኔ ኦሮምኛ የሚናገር አሸባሪ ህወሓት ነው የሚለውን እሳቤ ተገንዝቧል፣ አሸባሪ ህውሓት ነኝ ያለው እራሱ ሸኔ ነው፤ በዚህም ማንነቱ ለሕዝቡ ግልጽ ሆኖለታል።

ኦሮሞን ሲያጋጭ የነበረው ሸኔ ህወሓትን ወክሎ እንደነበር አሁን የአደባባይ ሚስጥር ሆኗል ሲሉ ገልጸዋል።

ኦሮሞን ከሌሎቹ ወንድሞቹ ጋር እንዲጣላና ግጭት ውስጥ እንዲገባ ያደረገው አሸባሪው ህወሓት ነው፥ ጉዳዩን የፈጸመው ደግሞ አሸባሪው ሸኔ ነው ብለዋል።

በመሆኑም ሸኔና ህወሓት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች መሆናቸውን ህዝቡ አሁን በግልጽ ሊገነዘበው እንደሚገባ አመልክተዋል።

ሁለቱም የሽብር ቡድኖች አረመኔዎች ናቸው፣ ይሄንን ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆኑ የዓለም ሕዝብ ያውቀዋል ያሉት አቶ ታዬ ፥ የሽብር ቡድኖቹ በሰው ልጆች ላይ ግፍ መፈጸማቸውን አስታውቀዋል።

አሸባሪው ህወሓት ሰው አኮላሽቷል፣ እግር ቆርጧል፣ ጥፍር ነቅሏል።

በተመሳሳይም አሸባሪው ሸኔ ህጻናትን ገድሏል፣ የሦስት ወር ሕጻንን አርዷል፣ ባል አቁሞ ሚስትን ደፍሯል፣ ልጆች ፊት አባት ረሽኗል፣ ሰው አቃጥሏል  ማለታቸውን ኢፕድ ዘግቧል።