አሸባሪው ህወሓት ቡድን ወደ ትግራይ ክልል ሊያስገባ የነበረው አደገኛ ዕፅ ተያዘ

ነሐሴ 19/2014 (ዋልታ) አሸባሪው የሕወሓት ቡድን ከአዲስ አበባ እስከ ሚሌ ኔትወርክ በመዘርጋት በአፋር ክልል በኩል ወደ ትግራይ ክልል ሊያስገባው የነበረ በርካታ ኩንታል አደገኛ ዕፅ በኅብረተሰቡ ጥቆማ እና በፖሊስ ብርቱ ክትትል ዛሬ መያዙን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አስታወቀ።

ሁለት ተጠርጣሪዎች በሰሌዳ ቁጥር አ.አ ኮድ 3-A40101AA ቶዮታ ዶልፊን ተሽከርካሪ ላይ አደገኛ ዕፁን ጭነው ሲያጓጉዙ በኅብረተሰቡ በተሰጠው ጥቆማ መሰረት ከሌሎች የፀጥታና ደኅንነት አካላት ጋር በመቀናጀት በቁጥጥር ስር ማዋሉን ነው የፌደራል ፖሊስ የገለጸው።

ከአደገኛ ዕፁ በተጨማሪ ለእኩይ ዓላማ ማስፈፀሚያ ሊውል የነበረ 2 ሚሊዮን 370 ሺሕ ብር መያዙንም ገልጿል።

በሕወሓት የሽብር ቡድን አባልነት ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉት ሁለቱ ተጠርጣሪዎች በሚጠየቁበት ጊዜ አደገኛ ዕፁን የእርዳታ እህል የጫኑ ተሽከርካሪዎችን በመጠቀም ወደ ትግራይ ክልል ለማስገባት እንደሆነ ተናግረው ዕፁን ለመቀበል የተዘጋጀ ቡድን እንዳለም ጠቁመዋል።

ፖሊስም ይህንን ቡድን በቁጥጥር ስር ለማዋል በክትትል ላይ መሆኑን አስታውቋል።

ይህ የሽብር ቡድን ዕፁን ሊያስተላልፍ የነበረው እንደለመደው የትግራይ ወጣቶችን በዕፅ አደንዝዞ ወደ ጦርነት ለመማገድ እንደነበረ በቁጥጥር ስር የዋሉት ተጠርጣሪዎቹ ተናግረዋል።

ይህ አደገኛ ዕፅ የተያዘው በህዝቡ ጥቆማና ቀና ትብብር በመሆኑ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ላቅ ያለ ምስጋናውን እያቀረበ በየትኛውም ደረጃ የሚወጠኑ መሰል የወንጀል ተግባራትን ለመቆጣጠር ህብረተሰቡ ከፀጥታ አካላት ጋር ተገቢውን ቅንጅት በማድረግ የዜግነት ድርሻውን እንዲወጣ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጥሪውን ያቀርባል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW
ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth
ዩቲዩብ https://www.youtube.com/c/WaltaTV/featured
ቲዊተር https://twitter.com/walta_info
አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን!