አሸባሪው ህወሓት የቀደመ ታሪካዊ መሰሪነቱን በመድገም ረሃብን በዋነኛ የትግል ስልትነት እየተጠቀመበት ይገኛል- ዶክተር ዲማ ነገዎ

                                         ዶክተር ዲማ ነገዎ

ሰኔ 25/2013 (ዋልታ) – አሸባሪው የህወሓት ቡድን ለትግራይ ህዝብ ወገንተኛ በመምስል የቀደመ ታሪካዊ መሰሪነቱን በመድገም ረሃብን በዋነኛ የትግል ስልትነት እየተጠቀመበት እንደሚገኝ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ዶክተር ዲማ ነገዎ አስታወቁ፡፡

ዶክተር ዲማ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፣ አሸባሪው ህወሓት ለትግራይ ህዝብ ወገንተኛ በመምስል የቀደመ ታሪካዊ መሰሪነቱን ለመድገም ረሃብን ዋነኛ የትግል ስልትነት እየተጠቀመበት ይገኛል፤ ቡድኑ በአሁኑ ወቅት የትግራይ ክልልን የማስተዳደር ቁመና አልተላበሰም፡፡

አሸባሪው ህወሓት ትናንት ሥልጣን ላይ በነበረበት ወቅት ያልፈታውን ውስብስቡን የትግራይ ችግር ዛሬም በወታደራዊ አስተሳሰብ ለመፍታት ጥረት እያደረገ ይገኛል ያሉት ዶክተር ዲማ፣ ሂደቱ እንደ ትናንቱ የሥልጣን ጥሙን ከማርካት በዘለለ በየትኛውም ስሌት አዋጭ አይደለም፤ ለትግራይ ህዝብ ችግርም ዘላቂ መፍትሄ አያመጣም ብለዋል፡፡

ቡድኑ እንደ ፕሮፓጋንዳ መሳሪያ የሚጠቀመው ሰው ሰራሽ ረሃብ ከኢትዮጵያ መንግሥት ቁጥጥር ውጪ አይደለም ያሉት ዶክተር ዲማ፣ በአካባቢው የተፈጠረው የጸጥታ ችግር የድጋፉን ሁኔታ አዳጋች በማድረጉ እንጂ መንግሥት በሚያደርገው ድጋፍና ከውጭ በሚመጡ ውስን ድጋፎች በመታገዝ ረሃቡን ለመቆጣጠር እንደሚቻል አስታውቀዋል፡፡

“አሸባሪው ቡድን ለትግራይ ህዝብ ወገንተኛ በመምስል በአንድ በኩል ወጣቱን ለፍሬ አልባ ጦርነት ይማግዳል በሌላ በኩል ደግሞ ‹‹ተጠቅተሃል፣ ተጎድተሃል›› በማለት በህዝቡ ውስጥ ከፍተኛ ጥላቻ ይዘራል” ብለዋል፡፡