አሸባሪው ህወሓት የትግራይ ሕዝብ ዋነኛ ጠላት ነው

ነሀሴ 14/2013 (ዋልታ) – አሸባሪው ህወሓት ለትግራይ ሕዝብ ዋነኛ ጠላት ነው ሲሉ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር አብርሃም በላይ ተናገሩ።

በአዲስ አበባ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ለአገር መከላከያ ሠራዊት ደም በመለገስ አጋርነታቸውን ገልፀዋል።

ዶክተር አብርሃም ደም ልገሳው የትግራይ ተወላጆች ‘በኢትዮጵያዊነታችን የማንደራደር መሆናችንን እንዲሁም ኢትዮጵያን አፅንተን ለማስቀጠል ያለንን ቁርጠኝነት የምናሳይበት ነው’ ሲሉ ተናግረዋል።

‘አሸባሪው ህወሓት የትግራይን ሕዝብ አይወክልም’ ያሉት ዶክተር አብርሃም ቡድኑ የሚያራምደው አጀንዳ የሕዝብ ሳይሆን የራሱን ነው ብለዋል።

የትግራይ ሕዝብ ኢትዮጵያን የሚያስቀጥል እንጂ የሽብር እንቅስቃሴ ደጋፊም አይደለም ነው ያሉት።

የሽብር ቡድኑ እኩይ ተግባር እንዳይሳካ የኢትዮጵያ ሕዝብ በሚንቀሳቀስበት ጊዜ ተጋሩ ግንባር ቀደም ሆኖ መንቀሳቀስ እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

ተጋሩ ኢትዮጵያን የሚያፀኑ እንጂ የሚያፈርሱ ቡድኖች አካል ሆኖ አያውቅም ያሉት ዶክተር አብርሃም ፤ከመከላከያ ሠራዊት ጎን ሆነን አሸባሪውን ቡድን ለማጥፋት በጋራ እንደቆምን የደም ልገሳው ቁርጠኝነትን ያሰያል ብለዋል።

እንደ አሸባሪው ህወሓት ለትግራይ ሕዝብ ዋነኛ ጠላት የለም ፤ በምንም መልኩ የትግራይ ሕዝብ የዚህ የሽብር ቡድን አጀንዳ ማስፈጸሚያ አይሆንም ሲሉም ተናግረዋል።

የጥፋት ሀይሉ በተደጋጋሚ የተዘረጉለትን የሠላም እጆች በመግፋት ለትግራይም ሆነ ለኢትዮጵያ ሕዝብ አሁንም ችግር ሆኖ ቀጥሏል ያሉት ደግሞ የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሀፍታይ ገብረ እግዚአብሄር ናቸው።

የኢትዮጵያ ችግር የሆነውን አሸባሪ ቡድን ኢትዮጵያዊያን ከጫፍ እስከ ጫፍ ተባብረን የመደምሰሱን ስራ ማረጋገጥ ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።