“አሸባሪው ሕወሓትን ከማስወገድ ውጭ ሌላ ምርጫ የለም” የኢዜማ ም/ሊቀመንበር

የኢዜማ ም/ሊቀመንበር ጫኔ ከበደ (ዶ/ር)

ጥቅምት 22/2014 (ዋልታ) ኢትዮጵያን ለመታደግ እስከመጨረሻ ተዋግቶ ጠላት አደብ ከማስያዝ ውጭ ሌላ አማራጭ እንደሌለ የኢዜማ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር ጫኔ ከበደ (ዶ/ር) አስታወቁ።

አገሪቱን ለ27 ዓመታት ሲያስተዳድር የነበረው የሕወሓት አሸባሪ ቡድን የበላይነቱን በኃይል ለማስቀጠል አገሪቱን በቀጥታ ጦርነት ብሎም በዲፕሎማሲ በቅጠረኞቹ በኩል በፈጸማቸው በደሎች በዜጎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል ያሉት ጫኔ ከበደ (ዶ/ር) ከአሁን በኋላ ቡድኑን ተዋግቶ ወደ መቃብር ከመሸኘት ውጭ ሌላ አማራጭ የለም ብለዋል።

“በመኖርና ባለመኖር መስቀለኛ መንገድ ላይ ሆነን ቡድኑ በዘራቸው የዘረኝነት አስተሳሰብ፣ ጥርጣሬና መርዛማ ጥላቻ ይዘን በእንዲሁ በጨበጣ አገሪቱን ማስቀጠል ወደ ከፋ ቀውስ ይወስደናል” በማለት ስጋታቸውን የገለጹት የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበሩ፣ ምንም እንኳ ስር የሰደደው የቡድኑ አመለካከትና አስተምሮ በአንድ ጀምበር ማጥፋት አዳጋች ቢሆንም የሽብር ቡድኑን ግን በአንድነት ማጥፋት እንደሚቻል ገልጸዋል።

“ትናንት ያስተዳደራትና ባለውለታዋ አትዮጵያን ካላፈረስኩ ሰላም የለኝም” የሚል ቡድን አስተሳሰቡን ቀይሮ ወደ ውይይቱ ይመጣል የሚል እምነት እንደሌላቸው የተናገሩት ምክትል ሊቀመንበሩ፣ ቡድኑ በተለያዩ ጊዜያት እድል ተሰጥቶት ያልተጠቀመ፣ በተግባርም ተፈትኖ የወደቀ ቡድን ከመሆኑም በላይ አሁን በሚያራምደው አደገኛ አቋሙ ይቅርና ለቀሪው ሕዝብ ለትግራይ ሕዝብም የሚበጅ ቡድን አይደለም ብለዋል።

አሻባሪው ሓወሓት አገር የማፍረስ ቅዠቱ ትናንት ያልተሳካ ዛሬም የቁርጥ ቀን የኢትዮጵያ ልጆች እያሉ እንደማይሳካለት በልበ ሙሉነት የተናገሩት ጫኔ ከበደ (ዶ/ር)፣ ሆኖም ግን አገሪቱ እንዳትረጋጋና የልማት ሥራዎች በተሳካ ሁኔታ እንዳይከናወኑ የማደናቀፍ ሴራውን አጠናክሮ ከማስቀጠል ወደኋላ ስለማይል የቡድኑ ድርጊትና አስተሳሰብ በተጠና መልኩ ማኮላሸት ያስፈልጋል ማለታቸውን ኢፕድ ዘግቧል።