አሸባሪው ሕወሓት ለመዝመት ፈቃደኛ ያልሆኑ ልጆች ወላጆችን እያሰረ መሆኑ ተጠቆመ

ሚያዝያ 26/2014 (ዋልታ) አሸባሪው የሕወሓት ቡድን እየተካሄደ ባለው ጦርነት ልጆቻቸው ያልዘመቱ ወላጆችን እያሰረ እንደሚገኝ የቤተሰብ አባላት ተናገሩ።

ቢቢሲ ያነጋገረው አንድ የትግራይ ተወላጅ ልጆች ለመዝመት ፈቃደኛ ሳይሆኑ በመቅረታቸው ወላጅ አባቱ እና አጎቱ እንደታሰሩ ገልጿል።

ለራሱና ለቤተሰቡ ደኅንነት ሲል ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀው ወጣት “ቢያንስ ከቤተሰብ አንድ ሰው ለውትድርና መላክ የሚል ሕግ አለ” ይላል።

ይህ በአሁኑ ወቅት ከትግራይ ክልል ውጪ የሚገኘው ወጣት “አባቴን ልጅህን አምጣህ አሉት፤ ማምጣት ስላልቻለ ለአንድ ወር አሰሩት፤ ከዚያ ደግሞ ወንድሜን እንዲያመጣ ብለው ለቀውት ነበር፤ አሁን ያለበትን ሁኔታ ባላውቅም ለመጨረሻ ጊዜ በስልክ ሳገኛቸው አባቴን አስረውት ነበር” በማለት ገልጿል።

ይህ ወጣት እንደሚለው “አዋቂ የሆነው ወንድሙ በዚህ ጦርነት ተሳታፊ የመሆን ፍላጎት የለውም፤ ወንድሜ እኮ ትልቅ ነው፤ ከፈለገ የአባቴን ፍቃድ ሳይጠይቅ ይሄድ ነበር፤ የያዙት ግን አባቴን ነው” በማለትም ለቢቢሲ ተናግሯል።

የባይቶና ዓባይ ትግራይ ፓርቲ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ ክብሮም በርሀ ታናሽ እህታቸው ለመዝመት ፍላጎት ስለሌላት ወላጅ እናታቸው በሕወሓት መታሰራቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ሌላኛው የትግራይ ክልል ነዋሪ በአሁኑ ወቅት በክልሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች እንዳሉ ገልጾ ከእነዚህም መካከል አንዱ ወላጆች ልጆቻቸውን ለትግል እንዲልኩ መገደዳቸው መሆኑን ገልጿል።