አሸባሪው ሕወሓት ለሚያደርገው ትንኮሳ እርምጃ የሚወሰድበት አቅጣጫ ተቀመጠ

ጥር 20/2014 (ዋልታ) ሽብርተኛው የሕወሓት ቡድን ለሚያደርገው ትንኮሳ የመከላከያ ሰራዊትና የክልል ጸጥታ ኃይሎች በጥናት ላይ ተመስርተው እርምጃ የሚወስዱበት አቅጣጫ ተቀመጠ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተመራው የፌዴራል ጸጥታ ምክር ቤትና የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች ውይይት በአገራዊ ጸጥታ ሁኔታ ላይ የቀጣይ አቅጣጫ ላይ ትኩረት አድርጓል።
በምክክሩም አገሪቱ አሁን ያለችበት አንጻራዊ ሰላምና ጸጥታን አጠናክሮ ማስቀጠል፣ ህገ ወጥ እንቅስቃሴዎችን ማስቆምና በጦርነቱ ምክንያት የተፈጠሩ ኢ-መደበኛ አደረጃጀቶችን ቅርጽ ማስያዝ እንደሚገባ ከስምምነት ተደርሷል።
በተለይ ሽብርተኛው የሕወሓት ቡድን የሚያደርገውን ትንኮሳን ተከትሎ እርምጃዎች በሚወሰድበት አግባብ አቅጣጫ ተቀምጦለታል።
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክር ተመስገን ጥሩነህ በሀገሪቱ ቀጣይ ስጋት ሊሆኑ የሚችሉ ጉዳዮች ከወዲሁ መስመር የማስያዝና የማስተካካያ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ አንስተዋል።
ህገወጥ የመሳሪያ ዝውውር፣ የኮንትሮባንድና መሰል እንቅስቃሴዎች የተገመገሙ ሲሆን በውስጥ ያሉ ችግሮችን ከመፍታት ባለፈ ቀጣናው ላይ ሰላምን ማስጠበቅ እና ሀገራዊ ግንኙነትን ማጠናከር ላይ አቅጣጫዎች ተቀምጠዋል ብለዋል።
የአገር መከላከያ ሚኒስትሩ አብርሃም በላይ (ዶ/ር) በበኩላቸው የአሸባሪ ቡድኖችን እንቅስቃሴ በመገምግም እርምጃ መውሰድ የሚቻልበት ሁኔታን ከመመልከት ባለፈ አሸባሪዎች ላይ እርምጃ መውሰድን የተመለከተ አቅጣጫ ተቀምጧል ነው ያሉት።
የተቀመጡ አቅጣጫዎችም ሆነ የተደረሰባቸው ስምምነቶችን የፌዴራልም ሆነ የክልል የጸጥታ አካላትና አስተዳደሮች በየደረጃው ተግባራዊ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል ሲል ኤፍቢሲ ዘግቧል።