ኅዳር 27/2014 (ዋልታ) አሸባሪው ሕወሓት በፈጸመውና እየፈጸመ ለሚገኘው ከባድ ኢሰብኣዊ ድርጊት ማዕቀብ እንዲጣልበት ለአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ደብዳቤ ተጻፈ።
አሜሪካ በሽብር ቡድኑ ላይ በአስቸኳይ ማዕቀቡን ተግባራዊ እንድታደርግ የጠየቀው በአሜሪካ የኢትዮጵያዊያን ፐብሊክ ጉዳዮች ኮሚቴ ነው።
ኮሜቴው በደብዳቤው “በአሸባሪው ሕወሓት ላይ በአሜሪካ መንግሥስት ሊጣሉ የታሰቡት ማዕቀቦች በአፋጣኝ እንዲተገበሩ በአክብሮት እንጠይቃለን” ብሏል፡፡
ኮሚቴው ጥያቄውን ያቀረበው ለአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ይፋዊ ደብዳቤን በመጻፍ ነው፡፡
ኮሚቴው ለሚኒስቴሩ ደብዳቤውን ለማጻፍ የተገደደው ሕወሓት በፈጸመውና እየፈጸመ በሚገኝ ከባድ ኢሰባኣዊ ድርጊት ምክንያት መሆኑን ገልጿል ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ብዙ የአሸባሪው ሕወሓት አመራር አባላት ከፍተኛ ሃብትና ካፒታል በውጭ አገር አላቸው ያለው ኮሚቴው ሆኖም አሜሪካም ሆኑ ሌሎች ተባባሪዎቿ በአሸባሪው ሕወሓት አባላት ላይ ያነጣጠረ ማዕቀብ አልተገበሩም ነው ያለው።
በእነዚህ ግለሰቦች እና ድርጅቱ ላይ ማዕቀብ መጣል፤ በኢትዮጵያ የሽብር ድርጊትን በመከላከል ንጹሃንን ከአሰቃቂ ጥቃት መታደግ ይቻላል ሲል አስረድቷል፡፡
አሜሪካ ከዚህም በተጨማሪም ወቅታዊ የኢትዮጵያን ሁኔታን ታሳቢ ባደረገ መልኩ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋን እንድታራምድ ነው የኢትዮጵያዊያን ፐብሊክ ጉዳዮች ኮሚቴ የጠየቀው።