አሸባሪው ሕወሓት ትምህርት ቤቶችን ማውደም ኢትዮጵያ ብቁ አገር ተረካቢ ትውልድ እንዳይኖራት የሚደረገው ሴራ አካል ነው

ዮሃንስ በንቲ (ዶ/ር)

ታኅሣሥ 4/2014 (ዋልታ) አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በትምህርት ቤቶች ላይ ያደረሰው ውድመት ኢትዮጵያ ብቁ አገር ተረካቢ ትውልድ እንዳይኖራት የሚደረገው ሴራ አካል መሆኑን የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር አስታወቀ።

ማኅበሩ ውድመት የደረሰባቸውን የትምህርት ተቋማትን መልሶ ለማልማት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡

አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በወረራ ይዟቸው በቆየባቸው አካባቢዎች በዋናነት የሕዝብ መገልገያ ተቋማት ላይ ከፍተኛ ውድመትና ዘረፋ የፈጸመ ሲሆን ከነዚህም የነገ አገር ተረካቢ ህጻናትን የሚያፈሩ ትምህርት ቤቶች ዋነኞቹ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ፕሬዝዳንት ዮሃንስ በንቲ (ዶ/ር) ትምህርት ቤት ታዳጊዎች ቀጣይ የህይወት ጉዟቸውን የሚለዩበት፣ የሚታነጹበትና በአስተሳሰብም ሆነ በተግባር እንዲበቁ የሚታገዙበት እንጂ የፖለቲካ ማስፈጸሚያ ተቋም አይደለም ብለዋል።

ትምህርት ቤት በጦርነት ወቅት ከማይነኩ ተቋማት መካከል አንዱ መሆኑን ያነሱት ፕሬዝዳንቱ አሸባሪ ቡድኑ በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች የትምህርት ተቋማትን ከማውደም ባሻገር በርካታ የትምህርት መገልገያ ቁሳቁስን መዝረፉንና ይህም የአሸባሪ ቡድኑን የአስተሳሰብ ዝቅጠት እንደሚያሳይ ተናግረዋል፡፡

አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በትምህርት ተቋማት ላይ ያደረሰውን ውድመት የዓለም ዐቀፉ ማህበረሰብ በግልጽ ሊያወግዘው ይገባል ነው ያሉት፡፡

ማኅበሩ በቅርቡ በአማራ ክልል የወደሙ ትምህርት ቤቶችን መልሶ ለማቋቋም የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ የ50 ሺሕ ብር ደጋፍ ማድረጉን ገልጸው በቀጣይም በተመሳሳይ ለአፋር ክልል ድጋፍ እንደሚያደርግ ጠቅሰዋል፡፡

ድጋፉም ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም የማህበሩ ፕሬዝዳንት መናገራቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡