አሸባሪው ሕወሓት ከናዚ የበለጠ ግፍ ፈፅሟል ሲሉ የታሪክ ምሁራን ገለፁ

ጥቅምት 26/2014 (ዋልታ) የሕወሓት የሽብር ቡድን ከምስረታው ጀምሮ ለአገር እና ለወገን ግድ ያልነበረውና በኢትዮጵያዊያን ላይ ከናዚ የበለጠ ግፍ የፈፀመ ነው ሲሉ የታሪክ ምሁራን ገለፁ።

ከዋልታ ጋር ቆይታ ያደረጉት የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ምሁራን እንደተናገሩት አሸባሪው ሕወሓት ልዩነት ላይ መሰረት ያደረገ ማኅበረሰብ መፍጠር እና በወንድማማቾች መካከል አለመተማመን በመዝራት የሥልጣን ዘመኑን ማራዘም ዓላማው እንደነበረ ተናግረዋል።

በቦንጋ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ እና የቅርስ አስተዳደር መምህሩ ሰለሞን ኪዳኔ ሕወሓት የሰራው ግፍ ናዚ ከሰራው ግፍ ይበልጣል ብለዋል።

ናዚ አሰቃቂ ተግባሩን ሲፈጽም የነበረው በሌሎች አገራት ዜጎች ላይ ነበር ያሉት መምህር ሰለሞን አሸባሪው ሕወሓት ግን የገዛ ወገኖቹ ላይ ያደረሰው ግፍ እና በደል በታሪክ እጅግ አሳፋሪ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

የሽብር ቡድኑ ሕወሓት በታሪክ ውስጥ ያሉትን ጥቃቅን ግጭቶች በማጉላት የራሱን ጥቅም ሲያመቻች ነበር የሚሉት መምህር ሰለሞን ነገር ግን ኢትዮጵያን ለመከፋፈል ባሰበው ልክ አልተሳካለትም ብለዋል።

በተለይም ኢትዮጵያ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በነበረችበት ጊዜ ሁሉ ምዕራባውያኑ ከጎናችን ሆነው እንደማያውቁ ጠቅሰው አሁንም በኢትዮጵያ ውስጣዊ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ቀውስ በመፍጠር የአፍሪካ ራስን የመቻል ተምሳሌት እንዳትሆን እያሴሩ ነው ይላሉ፡፡

ሌላው የታሪክ እና የቅርስ አስተዳደር መምህር ተክለአብ ቦሎ (ዶ/ር) በበኩላቸው አሸባሪው ሕወሓት ማኅበረሰቡን እርስ በእርሱ በጥርጣሬ ሸብቦ ይዞ ሥልጣኑን ማራዘም እና ሀብት ማካበት ብቸኛ ዓላማው እንደሆነ ገልጸዋል።

ቡድኑ የራሱን ጥቅም እስካስከበረ ድረስ ለወጣበት ማኅበረሰብ እንኳን ግድ የለውም ያሉት የታሪክ ምሁሩ ያሳደገውን እና ጡት የጠባበትን ማኅበረሰብ እንኳን ከመግደል እንደማይመለስ ብዙ ጊዜ አሳይቷል ብለዋል።

አገር የማይቀድም ከሆነ ሰው ያለአገሩ ባዶ ነው ያሉት መምህራኑ የሚለያዩንን ነገሮች ወደጎን በመተው እንደነታችንን በማጠናከር አገራችንን ማስቀጠል ይገባናል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በሔለን ታደሰ (ከቦንጋ)

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት፦
የአማርኛ ፌስቡክ ገፃችንን ይወዳጁ ይከተሉ
ከአረብኛ ፌስቡክ ገፃችን ጋርም ይጓዙ
የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ
የዩቲዩብ ቻናላችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ
የትዊተር ገፃችንን ይከተሉ
አብራችሁን ስለሆናችሁ ደስተኞች ነን!