አሸባሪው ሕወሓት ከ3 ሺሕ በላይ የኅብረት ሥራ ማኅበራትና ዩኒየኖች ላይ ዘረፋና ውድመት አድርሷል

ጥር 19/2014 (ዋልታ) በአማራ ክልል አሸባሪው የሕወሓት ቡድን 3 ሺሕ 228 የኅብረት ሥራ ማህኅበራትንና ዩኒየኖችን መዝረፉንና ማውደሙን የክልሉ የኀብረት ሥራ ማኅበራት ማስፋፊያ ኮሚሽን አስታወቀ።
በድኑ በሕዝብ ሐብትና ንብረት ላይ ያደረሰው ዘረፋና ውድመት ከ25 ቢሊየን ብር በላይ እንደሚገመት ኮሚሽኑ ገልጿል።
የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ልጃለም ገዳሙ ቡድኑ 3 ሺሕ 127 የኅብረት ሥራ ማኅበራትን፣ 22 ዩኒየኖችንና 79 የዞንና የወረዳ ኅብረት ሥራ ማኅበራት አደራጅ ጽሕፈት ቤቶችን መዝረፉንና ውድመት ማድረሱንም ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም ስምንት የእርሻ ትራክተሮችን ጨምሮ በርካታ የመስክ ተሽከርካሪዎችን፣ የዓሳ ማስገሪያ ጀልባዎችንና ሌሎች የቢሮ መገልገያ ቁሳቁስን ዘርፏል፣ ያልቻለውን ደግሞ አውድሟል ነው ያሉት ኃላፊው።
በኅብረት ሥራ ማኅበራቱ ተቀጥረው ሲሰሩ የነበሩ ከ9 ሺሕ በላይ ወገኖች ከሥራ ገበታ ውጭ እንዲሆኑ ማድረጉንም አስረድተዋል።
ማኅበራቱን ወደ ሥራ ለማስገባት ክልሎች፣ አቅም ያላቸው አቻ ዩኒየኖችና የህብረት ስራ ማኅበራት እንዲሁም መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽንም ድጋፍና እገዛ እንዲያደርግ ጥያቄ ቀርቦ ምላሽ እየተጠበቀ መሆኑን ተናግረዋል።
ማኅበራቱን፣ ዩኒየኖችንና ጽሕፈት ቤቶችን ወደቀደመ ሥራቸው ለመመለስ 30 ቢሊየን ብር የሚጠጋ ገንዘብ እንደሚያስፈልግም ማብራራቱን ኢዜአ ዘግቧል፡፡