አሸባሪው ሕወሓት ዳግም የከፈተውን ጦርነት የሚያወግዝ ሰላማዊ ሰልፍ በዋሺንግተን ዲሲ እየተካሄደ ነው

ጳጉሜ 1/2014 (ዋልታ) በአሜሪካ ዋሺንግተን ዲሲ አሸባሪው ሕወሓት ዳግም የከፈተውን ጦርነት የሚያወግዝ ሰላማዊ ሰልፍ እየተካሄደ ነው።

ሰልፉ “በአገር ሕልውናና አንድነት አንደራደርም!” በሚል መሪ ሀሳብ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ፊት ለፊት እየተከናወነ ይገኛል።

ሰልፉ አሸባሪው ሕወሓት ዳግም የከፈተውን ጦርነት ለማውገዝና የአገርን ሕልውና ለማስጠበቅ እየተሳተፉ ላሉ የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ የጸጥታ ኃይሎችና ዜጎች ድጋፍና አጋርነትን የመግለጽ አላማ እንዳለው የሰላምና አንድነት ለኢትዮጵያ ዲሲ ግብረ ኃይል ገልጿል።

የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያና ኤርትራ ላይ ያለውን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በመከባበርና በሁለትዮሽ የጋራ ጥቅም ላይ ያተኮረ እንዲሆን የሚያሳስቡ መልዕክቶች በሰልፈኞቹ ተላልፈዋል።

በሰላማዊ ሰልፉ ላይ ትውልደ-ኢትዮጵያውያንና ሌሎች የኢትዮጵያ ወዳጆች መሳተፋቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የሰላምና አንድነት ለኢትዮጵያ ግብረ ኃይል ሰልፉን ከአገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ጋር በትብብር እንዳዘጋጀውም ተገልጿል።