አሸባሪው ትሕነግ ቅርስን በማውደም ታሪክ ጠል ባህሪውን እያስመሰከረ መሆኑ ተገለጸ

ነሐሴ 26/2013 (ዋልታ) – አሸባሪው ትሕነግ ቅርስን በማውደም ታሪክን በማጥፋት ታሪክ ጠል ባህሪውን እያስመሰከረ ይገኛል ሲሉ የቅርስ ጥናት ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፈሰር አበባው አያሌው ገለጹ፡፡

ረዳት ፕሮፈሰር አበባው የአሸባሪው ትህነግ ቡድን በአሁኑ ወቅት የእምነት ተቋማትና ቅርሶችን እያወደመና እያረከሳቸው እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

በአማራ ክልላዊ መንግስት አራተኛው ክፍለ ዘመን ተገንብቶ ለህዝቡ አገልግሎት በመስጠት ላይ በሚገኘው ጨጨሆ መድሃኒአለም ቤተክርስቲያን ላይ አሻባሪው ህወሓት በከባድ መሳሪያ የቤተክርስቲያኑን ጣራ ግድግዳ በማፍረስ ያደረሰው ጥቃት ማሳያ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

በቤተክርስትያኑ ላይ ጉዳት ያደረሰውን የአሸባሪው ህወሓት ቡድንን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሊያወግዘው ይገባል ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፣ የሽብር ቡድኑ ድርጊት በባህሪው ከምስረታው አንስቶ ታሪክ ጠል መሆኑን ያስመሰከረ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የጨጨሆ መድሃኒያለም ቤተክርስትያን በአራተኛው ክፍለ ዘመን የተገነባና በርካታ የታሪክ መዛግብቶች እንደ ብራና መፅሐፍና የተለያዩ ቅርሶችን በውስጡ የያዘ ትልቅ ደብር እንደሆነ መግለፃቸውን ኢፕድ ዘግቧል፡፡