አሸባሪው ትሕነግ በአፋር የዘር ማጥፋት እየፈፀመ መሆኑን ክልሉ አስታወቀ

አሸባሪው ትሕነግ

ጥር 8/2014 (ዋልታ) አሸባሪው ትሕነግ በአፋር አብአላ በኩል በከፈተው ግንባር በንፁሃን ላይ ድጋሚ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ እየፈፀመ መሆኑን የክልሉ መንግሥት አስታወቀ፡፡

የሽብር ቡድኑ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ በአስቸኳይ መቆም አለበት ሲል መግለጫ ያወጣው የክልሉ መንግሥት በኪልበቲ ረሱ (ዞን ሁለት) አብአላ በኩል ከታኅሣሥ 10 ጀምሮ በከፈተው አዲስ ግንባር በተከታታይ እየተኮሰ ባለው ከባድ መሳሪያ ንፁሃን ዜጎችን መጨፍጨፉን ቀጥሏል ብሏል።

በዚህም ጋሊኮማን ጨምሮ በአራት ዞኖች ውስጥ በተለያዩ ወረዳዎች ያደረሰውን የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ በድጋሚ በአብአላና በመጋሌ እየደገመ ይገኛል ተብሏል።

ቡድኑ በከባድ መሳሪያ በታገዘ ድብደባው በርካታ ንፁሃን በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል፣ ቆስለዋል፣ በበርካታ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ደግሞ በጥቃቱ ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ለስደት ተዳርገዋል ነው ያለው።

የትግራይን ሕዝብ ከሁሉም ኢትዮጵያዊያን ጋር ለማናከስ ቆርጦ የተነሳው አሸባሪው ትሕነግ የአፋርና ትግራይ ሕዝብን በማናከስ እድሜውን ለማራዘም እየጣረ ነው ብሏል፡፡

ቡድኑ ዳግም ወረራ ለማካሄድ ጥረት እደረገ መሆኑን ያሳወቀው የአፋር ክልል ትናንትና ዛሬም በተለያየ መልኩ ተደራጅቶ በመምጣትና ከባድ መሳሪያዎችን በመተኮስ ንፁሃንን መግደሉንና ንብረት ማውደሙን ገልጿል፡፡

የምድር ድሮኖቹ አሁንም ቢሆን የሽብር ቡድኑን በሚገባው ቋንቋ እያናገሩት ነው፤ ወደ አፋር ክልል ዘልቆ እንዳይገባም ብርቱ ተጋድሎ በማድረግ ላይ ይገኛሉ ብሏል።

ቡድኑ ከጥፋት መንገዱ አለመታቀቡንና በአፋር በኩል እየፈፀመ ባለው የንፁሃን ጭፍጨፋ ምክንያት ጦርነቱ አለመቆሙን አሳውቋል፡፡