አሸባሪው የህወሓት ቡድን ሀገር የማፍረስ ፍላጎት በኢትዮጵያ ልጆች የተባበረ ክንድ ድባቅ ይመታል- የአፋር ክልል ሴቶች

ሐምሌ 24/2013 (ዋልታ)- የአሸባሪው የህወሓት ቡድን ሀገር የማፍረስ ፍላጎት በኢትዮጵያ ልጆች የተባበረ ክንድ ድባቅ ይመታል ሲሉ የአፋር ክልል ሴቶች ገለጹ።

ከክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የተወጣጡ ሴቶች  በሰመራ ከተማ እያካሄዱ ባሉት ሰላማዊ ሰልፍ የአሸባሪውን ህወሓት ቡድንን ሀገር የማፍረስ ሴራ ከመከላከያና ልዩ ሀይሎች ጎን በመሰለፍ ለማክሸፍ ቁርጠኛ መሆናቸውን በላቀ የሀገር ፍቅር ስሜት እየገለጹ ነው።

በአሸባሪው ፊት-አውራሪነት በንጹሃን ህጻናት፣ ሴቶችና አረጋውያን ላይ የሚፈጸመውን  ግድያ የአለም ህዝብ ሊያወግዘው ይገባል ብለዋል።

“ትውልዱ የአባቶቻችንን አደራ አያጥፍም፣ ኢትዮጵያን ለማዳን እዘምታለሁ፣ የጁንታው ሀገር የማፍረስ ፍላጎት በልጆቿ የተባበረ ክንድ ድባቅ ይመታል” ሲሉ መልዕክት እያስተላለፉ ይገኛሉ።

የክልሉ ሴቶች በአሸባሪው ህወሓት ላይ መንግስት በጀመረው የህልውና ዘመቻ እስ ከህይወት መስዋዕትነት በመከፈል ታሪካዊ አደራቸውን ለመወጣት ቁርጠኛ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።

ሰልፈኞቹ በአሁኑ ወቅት  በሰመራ ከተማ ዋና ዋና ጎዳናዎች በመዘዋወር  አሸባሪው የህወሃት ቡድን የጥፋት ድርጊት የሚያወግዙና የሀገር መከላከያ ሰራዊትን የሚደግፉ መልዕክቶችን ማስተላለፋቸውን ኢዜአ ዘግቧል።