አሸባሪዎችን በማስወገድ የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የሲዳማ ህዝቦች ቆርጠን ተነስተናል – አቶ ደስታ ሌዳሞ

ነሃሴ 14/2013 (ዋልታ) –  “ሀገር ለማፍረስ እየሰሩ ያሉትን አሸባሪዎቹ ህወሃትና ሸኔ በተባበረ ክንድ በማስወገድ የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የሲዳማ ህዝቦች ቆርጠን ተነስተናል” ሲሉ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ገለጹ።

የክልሉ ነዋሪዎች ለመከላከያ ሰራዊቱ ያላቸውን አጋርነት ለመግለጽ የድጋፍ ሰልፍ ዛሬ በሐዋሳ ከተማ አካሂደዋል።

በሰልፉ ላይ የተገኙት ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅቱ እንዳሉት፤ ሀገር ለማፍረስ የረጅም ጊዜ ህልም የነበረው አሸባሪው ህወሃት በስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት በተከተለው ከፋፍለህ ግዛ መርህ የልዩነት መርዝ ቢዘራም ያቀደው አልተሳካለትም።

በህዝብ ተቃውሞ ከስልጣን የተወገደው አሸባሪ ቡድን ውጥኑ በጥበበኛና ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን እንደመከነ ተናግረዋል።

“ኢትዮጵያዊያን አንድነታችንን በማጠናከር የእናት ጡት ነካሽ የሆኑ አሸባሪ ቡድኖች የፈጠሩትን ሀገር የማፍረስ አጀንዳ በአጭር ጊዜ በመቀልበስ የበለጸገች ሀገር የመገንባት ራዕያችን እውን ይሆናል” ብለዋል።

የአሸባሪው ህወሃት የሀሰት ፕሮፓጋንዳ በመቀበል በኛ ውድቀት ለመበልጸግ የቋመጡ የውጭ ሃይሎች ከታሪክ ሊማሩ እንደሚገባም ጠቁመዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

አንዳንድ ምዕራባዊያን ኢትዮጵያዊያን በአሸባሪው ቡድን ላይ እየወሰዱት ያለውን ሃገር የማዳን ትግል ከማደናቀፍ ሊቆጠቡ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

የሲዳማ ክልል ህዝብ የመከላከያ ሰራዊትን ለማጠናከር የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል።

የብልጽግና ፓርቲ የሲዳማ ክልል ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አብርሃም ማርሻሎ በበኩላቸው “ሀገር ለማፍረስ እየሰሩ ያሉት እየፈረሱ ኢትዮጵያ እያሸነፈች ትገኛለች” ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከአሸባሪ ቡድንና ከውጭ ጫና እስክትላቀቅ ድረስ የሲዳማ ህዝብ ያለ እረፍት የሚጠበቅበትን ሁሉ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የሰልፉ ተሳታፊዎች አሸባሪዎቹ እየፈጸሙት ባለው የባዳና የባዕዳን ተግባር መቆጣታቸውን ገልጸዋል።

የአገር መከላከያ ሰራዊትን መድፈር ወንጀል መሆኑን ገልጸው፤ መከላከያ ሰራዊትን ለማጠናከር ከሚደረገው ድጋፍ ባሻገር እስከ ግንባር ድረስ በመዝመት የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

የሰልፉ ተሳታፊዎች “እኔ ለሀገሬ ወታደር ነኝ፣ ከጀግናው መከላከያ ሰራዊት ጎን ነን፣ በሉዓላዊነታችን ተደራድረን አናውቅም፣ በኢትዮጵያ ላይ የተዘረጉ እጆች ይሰብሰቡ፣ እኛ ኢትዮጵያዊያን ፍላጎታችንን በምርጫ ካርዳችን ግልጽ አድርገናል፣ የህዳሴ ግድቡን ገንብተን እናጠናቅቃለን” የሚሉ መልዕክቶች ተላልፈውበታል።