አሸባሪ ህወሓትን ለማጥፋት የአሁኑ ትውልድ ታሪካዊ ኃላፊነት

አቶ ገዱ አንዳርጋቸው

ጳጉሜ 1/2013 (ዋልታ) የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ ገዱ አንዳርጋቸው ወራሪው የትህነግ ኃይልን ለመቅበር ብሎም ለመላው ኢትዮጵያ ስጋት ወደማይሆንበት ደረጃ ለማድረስ የአሁኑ ትውልድ ታሪካዊ ኃላፊነት አለበት ብለዋል።

የደሴ ከተማ አስተዳደር ወጣቶች በወቅታዊ የህልውና ዘመቻ አጀንዳዎች የምክክር መድረክ አካሂደዋል፡፡

በምክክር መድረኩ ላይ የተገኙት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው አሸባሪው ቡድን ከውጭ ጠላቶች ጋር ወግኖ ኢትዮጵያን ለማፍረስ እየሰራ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነቱን ጠብቆ ወራሪ ኃይሉ ለሀገርና ህዝብ ዳግም ስጋት በማይሆንበት መንገድ በመደምሰስ ህልውናውን የሚያስቀጥልበት ወቅት መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ አስተባባሪ አለሙ ስሜ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ወያኔን ብቻ ሳይሆን ተላላኪዎቹን ጭምር መቅበር ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) ሊቀመንበር በለጠ ሞላ (ረዳት ፕ/ር) አማራን ለማዋረድ የመጣው ኃይል አንድ ሆነን መመከት ይጠበቅብናል፤ ወጣቶችም መከላከያና ልዩ ኃይሉን መቀላቀል  እንደሚጠበቅባቸው አንስተዋል።

በመድረኩ የትህነግ ኃይል የህልውና አደጋነትና ምን መደረግ አለበት በሚሉ ጉዳዮች ላይ ጥናታዊ ፅሁፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

በውይይቱ ላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ ገዱ አንዳርጋቸው፣ በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ አስተባባሪ አለሙ ስሜ (ዶ/ር) እንዲሁም የደሴ ከተማ ከንቲባ አበበ ገብረመስቀል ተገኝተዋል።

በሳራ ስዩም