አብሮነት፣ ይቅርታና ምስጋና ላይ ትኩረቱን ያደረገ መርሃ ግብር በወራቤ ከተማ ተካሄደ

መጋቢት 9/2015 (ዋልታ) በስልጤ ማህበረሰብ ዘንድ ሲዘወተር የቆየው እና ይቅርታን የሚሰብከው “አውፋት” የተሰኘ መርኃ ግብር በወራቤ ከተማ ተካሂዷል፡፡

መርኃ ግብሩ በአብሮነት፣ ይቅርታና ምስጋና ላይ ትኩረቱን ያደረገ ሲሆን በማህበረሰቡ መካከል በተለያየ መነሾ የተቀበሩ ቁርሾዎችን በይቅርታ ማከም እንዲቻልና ለትውልድ ለማስተማር ያለመ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በመርኃ ግብሩ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የስራ እና ክህሎት ሚኒስትሯ ሙፈሪሃት ካሚል ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ በመካከላችን የተቀበረን መቃቃር እና ቁርሾዎችን በይቅርታ ማጥፋት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

ለዚህም በሀገሪቱ ይቅርታና ይቅርባይነትን የሚሰብኩ መልካም እሴቶችን እየመነዘሩ መጠቀም ያስፈልጋል ብለዋል::

የስልጤ ህዝብ ካሉት መልካም እሴቶች መካከል የሆነው የአውፋት እሴት በታሪክ አጋጣሚ በማህበረቦች መካከል አለመግባባትን የፈጠሩ አልያም ቁርሾን ያኖሩ ታሪኮችን በመፋቅ በይቅርታ እና አብሮነት እጅ ለእጅ የተያያዘ ማህበረሰብን ለመፍጠር የሚያግዝ እሴት መሆኑ ተመላክቷል::

ይህን መልካም እሴት አለመግባባትን የወለዱ እና መራራቅን ያመጡ ክስተቶችን ማከሚያ በማድረግ ሰላሟ የተረጋገጠች ኢትዮጵያን መፍጠር ያሻል ነው የተባለው::

በመርኃ ግብሩ ላይ በስልጤ ማህበረሰብ በሦስቱም ትውልዶች የነበሩ ቁርሾዎችን በይቅርታ ለማጣፋት በሚል የተበደሉ ይቅርታ የተጠየቁበት እንዲሁም ማህበረሰቡን በታሪክ አጋጣሚ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን ተሻግሮ ዛሬ ላይ እንዲደርስ ላስቻሉ የምስጋና መርኃ ግብር ተካሂዷል፡፡

ሄብሮን ዋልታው (ከወራቤ)