አትሌቶቻችን ያስመዘገቡት ውጤት ከተባበርን ምን ያህል ተጽዕኖ መፍጠር እንደምንችል አንዱ ማሳያ ነው – ርዕሰ መስተዳድር እርስቱ ይርዳ

ሐምሌ 21/2014 (ዋልታ) ከተባበርን እና አንድነታችንን ካጸናን ምን ያህል ተጽዕኖ መፍጠር እንደምንችል አንዱ ማሳያ የጀግኖቻችን ትጋት ነው ሲሉ የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር እርስቱ ይርዳ ገለጹ፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በአትሌቲክስ ቡድኑ የተገኘውን ዉጤት በማስመልከት የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

አትሌቶቻችን በአሜሪካ ኦሪገን ሲካሔድ በቆየው 18ኛው የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ባደረጉት ብርቱ ጥረት እውነተኛ የሀገር ፍቅር ስሜትን ተላብሰው የአገራቸውን ክብር በማስቀደም በዓለም አደባባይ ከፍ ብለን እንድንታይ አድርገውናል ብለዋል።

ዛሬ በሁሉም መስክ እየገጠመን ያለውን ፈተና ልክ እንደ አትሌቶቻችን ፊት ለፊት በመጋፈጥ ለድል የምንበቃበት እና የአገራችንን የቀደመ ታሪኳን የምናድስበት ቀን እሩቅ አይደለም ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ።

የአላማ ጽናት ጥልቅ የአገር ፍቅር ስሜት በአትሌቶቻችን ላይ እንዳየነው ሁሉ የአገርን ክብር እና የቀደመ የጀግንነት ታሪካችንን ማስቀጠል የዚህ ትውልድ ድርሻ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ከተባበርን እና መተኪያ የሌላት አገራችንን አስቀድመን አንድነታችንን ካጠናከርን ሊከፋፍለን እና ሊለያየን ያሰበ ጠላት አፍሮ እንደሚመለስም ገልጸዋል።